የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ኦዴፓና ኦነግን አስማሙ

75

አዲስ አበበባ ጥር 14/2011 የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲንና የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን አስማሙ።

ህብረቱ ያዘጋጀው የእርቀ ሰላም መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ጨምሮ አባገዳዎች፣ ሃ   ደ ሲንቄዎች (እናቶች)፣ ምሁራንና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተገኝቷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፥ “ህዝባችን በሰላም ወጥቶ መግባት ይፈልጋል፤ ከሰላም ውጭ ቤትም መላም የለንም፣ ፓርቲዎቹ በመካከላቸው ያለውን ችግር ካልፈቱ ወደ ቤት አንመለስም" በማለት ሁለቱ ፓርቲዎች ሰላም እንዲያወርዱ አሳስበዋል።

አባ ገዳዎቹ እና ሃደ ሲንቄዎቹ(እናቶች) ለእርቀ ሰላሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦ ኤም ኤን ቴሌቪዥን ዋና ዳይሬክተር ጀዋር መሐመድም "ሁሉም አካል ያለውን ሀቅ ፊት ለፊት በማምጣት መነጋገር አለበት" በማለት ሁለቱ ፓርቲዎች ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኛነት ሊያሳዩ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹም በአንድነት በመሆን ከኦሮሞ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች የቀረበላቸውን የእርቀ ሰላም ጥሪ መቀበላቸውን አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማእከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ የአንድ ሀገርና የአንድ አባት ልጆች በፖለቲካ ምክንያት መገዳደል እና አንዱ አንዱን ከሀገር ማባረር መቅረት አለበት ብለዋል።

ዶክተር አለሙ አክለውም፤ ከዚህ በኋላ "ጦርነትና አንዱ አንዱን ማዳከም አያስፈልግም" ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም በመድረኩ ፓርቲያቸውና መንግስት የደረሱትን ስምምነት አስታውሰዋል።

ችግሮችን ለመፍታትም ከዚህ ቀደም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውንም አስታውሰዋል።

አቶ ዳውድ አክለውም፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አሁንም ቢሆን ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፤ ለዚህም መንግስት ተቋማዊ ዋስትና እንዲሰጠን እንፈልጋለን ብለዋል።

ተሳታፊዎቹ የችግሩ መንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ ከተወያዩ በኋላም ኦዴፓና ኦነግ የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።

የኦነግ ጦር አባ ገዳዎች በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሰረት ትጥቁን ለአባ ገዳዎችና ለሀገር ሽማግሌዎች እያስረከበ ይግባ ሲሉም ተናግረዋል።

በእርቀ ሰላም ምክክሩ ስምምነት ላይ የተደረሱ ጉዳዮችን ለማስፈፀምም የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም በውይይት መድረኩ ከስምምነት ተደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም