የመንግስት አገልግሎትን ቀልጣፋና ውጤታማ ያደርጋል የተባለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ሊዘረጋ ነው

78

አዲስ አበባ  ጥር 14/2011 በኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎትን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል የተባለና "የመንግስት ኔትወርክ" የተሰኘ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መገናኛ አውታር ሊዘረጋ መሆኑን የኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዜጎች የሚሹትን የመንግስት አገልግሎት ለማጠናከር ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የታገዘ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ተገልጿል። 

ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት በሥሩ የሚያስተዳድረውንና ለመንግስት አገልግሎት እየሰጠ ያለውን "ወረዳኔት" የመገናኛ አውታር ለመተካት ያዘጋጀውን "የመንግስት ኔትወርክ (Goverment Backbone) የተሰኘውን ፕሮጀክት ምስረታና ወቅታዊ ዳሰሳ ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት አውደ ጥናት ዛሬ ተካሂዷል።

በዚህ ጊዜ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የመንግስት አገልግሎት ለመስጠት በተለምዶ ወረዳኔት የሚባል ቴክኖለጂን እየተጠቀመች ትገኛለች።

ይሁንና ቴክኖለጂው ዘመኑ የደረሰበትን ደረጃ የማይመጥንና መንግስት ለዜጎች መስጠት የሚፈልገውን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ለማዳረስ የማይችል መሆኑ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ማወቅ ተችሏል።

በመሆኑም "የመንግስት ኔትወርክ" የተሰኘ ሌላ ፕሮጀክት ለመመስረትና የመሰረተ ልማት አውታሩን ለማማሻል፤ በተጓዳኝም የብሔራዊ ዳታ ማዕከልን ለማስፋፋት ይቻል ዘንድ አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

አዲሱ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መገናኛ አውታር ብሄራዊ የታክስ አሰባሰብን ጨምሮ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ቀልጣፋና በውጤታማ ለማድረግ እንደዚሁም በኔትወርክ መሰረተ ልማት  ውስንነት የተገለሉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

በዚህም ለዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲሻሻሉ፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብትና የሰው ሃብት ምርታማነት የበለጠ እንዲጨምር  ያስችላል ሲሉም አብራርተዋል።

የዳሰሳ ጥናቱን ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የመንግስት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩንኬሽን ቴክኖሎጂ ኔትወርክ ልማት አስተዳዳር ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ኃይሉ እንደተናገሩት "ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የአገሪቷን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  እድገቶችን ማዘመን ያስፈልጋል።"

በተለይም አሁን ለመዘርጋት የታቀደው የመንግስት ኔትወርክ መሰረተ ልማት የመንግስት አገልግሎት ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆን፤ ግልፀኝነት እንዲሰፍንና የዜጎች ሁለንተዊ ተሳትፎ እንዲጎለብት ያስችላል።

በተለይም በሁሉም ተቋማት የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲኖር፣ የህዝብ ቆጠራን ለማካሄድ፣ የኢንተርት ቢዝነሶችን ለማከናወን፣ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ አገልግሎት ለመስጠት፣ የሃብት ብክነትን ለማስቀረትና የግብር አሰባሰብን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

ለዚህም የመንግስት ቁርጠኝነት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩንኬሽን ቴክኖሎጂ ፖሊሲ፣የፋይቨር ኦፕቲክስ መሰረተ ልማትና አለም አቀፍ ተሞክሮች መኖራቸው ምቹ ሁኔታ መሆኑን አብራርተዋል።

አቶ መኮንን ታያቸው የተባሉ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊች አሁን ለመዘርጋት የታቀደው የመንግስት የኔትወርክና ብሔራዊ ዳታ ማዕከል ማሻሻያ ስርዓት ኤሌክትሮኒክስ ምርጫንና ተጓዳኝ ጉዳዮችን ቢያካታት ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ዶክተር አብዮት ባዬ በስራ ላይ ያለው ወረዳኔት የህግ ማዕቀፍ እንዳልተዘጋጀለት ጠቁመው አሁን የሚዘረጋው የመንግስት ኔትወርክ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተውለት ወደተግባር መግባት ይኖርበታል ብለዋል።

አሁን ላይ የወረዳኔት ሲስተም በትምህርት ቤቶች፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በጤናና በግብርና ተቋማት እንዲሁም በባንኮችና በግብር አሰባሰብ ላይ እየተሰራበት ነው።

በአሁኑ ወቅት ባንኮችን ጨምሮ ወረዳኔትን ከ18 ሺህ በላይ ቀበሌች፣ከ5 ሺህ ቴክኒክና ሙያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 39 ሺህ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣18 ሺህ የሚሆኑ የጤና ኬላዎችንና በርካታ የጤና ተቋማትን በክልልና በፌደራል ደረጃ እንደሚጠቀሙ ከሚኒስትሩ መስሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም