በክልል ቀሪ የልማት ግቦችን ለማሳካት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ ተመለከተ

3593

ጋምቤላ ግንቦት 19/2010 በጋምቤላ ክልል የሁለተኛው የእደገትና ትራንስፎርሜሽን ቀሪ የልማት ግቦችን በቀጣይ ለማሳካት በየደረጃው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

በክልሉ በእቅዱ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም ላይ በጋምቤላ ከተማ ለአራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ውይይት ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡

በውይይት መድረክ  የተሳተፉ የንግዱ ማህብረሰብ እንዳሉት በክልሉ በአገልግሎት ዘርፎች በተለይም በጤና ተቋማት፤ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በማዘጋጃ ቤትና በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል  ወይዘሮ መብራት ብስራት በሰጡት አስተያየት በከተማዋ በንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትና በሆስፒታል አገልግሎት አሰጣት ላይ ችግሮች እንደሚታዩ ጠቆመው ” የክልሉ መንግስት መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል “ብለዋል፡፡

በከተማዋ የሚስተዋለውን የምግብ ፍጆታ እቃዎች በተለይም በስኳርና በዳቦ ዱቄት ላይ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ ንግድ በመቆጣጠር በኩልም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የሚታየው ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ጋር ተያይዞ በነዋሪው ህብረተሰብ ላይ የሚስተዋሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮችን ለመፍታት ሊሰራ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ ከጎግ ወረዳ ፍኝዶ ከተማ የመጡ አቶ አብዱልሰላም አወል ናቸው፡፡

“በወረዳው የሚስተዋለው የመንገድ ችግርና ከተማዋ በማስተር ፕላን ባለመመራቷ የባንክና ሌሎች አገልግሎቶችን ሊያገኙ ባለመቻላቸው ለችግር ተዳርገናል” ብለዋል፡፡

ወይዘሪት ትግዕስት እንደሪስ በበኩላቸው የከተማ ማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለበትና በተለይም ህገ-ወጥ የመሬት ዝርፊያና  በካርታ ላይ ካርታ እየተሰጠ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ታንኳይ ጆክ እንደተናገሩት በክልሉ የስኳርና የዱቄት እጥረት ችግር መኖሩን አምነው ቢሮው ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

በጋምቤላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱንና በቀጣይም አገልግሎቱን ለማሻሻል  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ጆን ጋች ናቸው፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሰናይ አኩዎር በበኩላቸው ” በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በትኩረት ይሰራል” ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የመንገድና የሆስፒታል ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል በቀጣዩ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ  መንግስት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለማሳካት ከያዘው እቅድ አንጻር  ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ለውጥ መታየቱን ገልጸዋል፡፡

” ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት አሁንም ብዙ ሊሰራ ይገባል “ብለዋል፡፡

የፌደራል መንግስት እቅዱን ለማሳካት በክልሉ ለሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚጠናከርም አስታውቀዋል፡፡