በክልሉ የዴሞክራሲ ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል

92

ጋምቤላ ጥር 14/2011 በጋምቤላ ክልል በዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ላክዳር ላክባክ ገለጹ፡፡

በክልሉ የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ ፎረም ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተመስርቷል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ላክዳር ላክባክ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን በክልሉ ለማራመድና በኅብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት  ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጎለብት ይደረጋል፡፡

በክልሉ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት፣አስተማማኝ ሰላም፣እኩልነትና የዜጎች ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነት ለመፍጠር በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት ለዴሞክራሲ ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ለዚህም ተቋማቱ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡

ፎረሙ በክልሉ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማጎልበት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሰራ አስገንዝበዋል፡፡  

በምስረታው ላይ የተገኙት አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ፎረሙ ተቋማቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት ጠቀሜታው ከፍተኛ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኡቦንግ ኡጁሉ እንዳሉት የተቋማቱ ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ በክልሉ የፍትህ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡

ለተግባራዊነቱም ሁሉም በትኩረት መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ በአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በተጠያቂነትና አሳታፊነት ላይ የተመሰረተ አደረጃጀት ለመፍጠር  ያግዛል ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት የማህበራዊ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወይናቱ አበራ ናቸው፡፡

የጎግ ወረዳ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አርያት ዳንኤል በበኩላቸው ፎረሙ በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ በማጠናከር የሴቶችንና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ የክልሉ ምክር ቤትን ጨምሮ ዘጠኝ ተቋማትን ያካተተ ሲሆን፣ በምስረታው ላይ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም