በህገ-ወጥ ቡና ያዘዋወረ አሽከርካሪ ተቀጣ

585

አምቦ ጥር 14/2011 በህገ-ወጥ መንገድ ቡና ሲያጓጉዝ ተገኝቷል ያለውን አሽከርካሪ በሦስት ዓመት እስራትና በ50 ሺህ ብር መቅጣቱን በምዕራብ ሸዋ ዞን የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ ፈዬራ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈበት ቶሌራ አያና የተባለ ግለሰብ ነው።

“ግለሰቡ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-27750 ኦ.ሮ በሆነ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪ በህገ-ወጥ መንገድ 817 ኪሎ ግራም ቡና ጭኖ ሲያዘዋውር ተገኝቷል” ብለዋል።

ቡናውን ከምስራቅ ወለጋ ዞን ወደ አዲስ አበባ በማጓጓዝ ላይ እንዳለ ጉደር ከተማ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ጨምረው ገልጸዋል ።

ፍርድ ቤቱ ትላንት ባዋለው ችሎት ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ቅጣቱ የተላለፈበት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል ።