በአግባቡ ያልተወገደ የህክምና መርፌ አግኝተው እርስ በእርስ በመወጋጋታቸው በተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል

596

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቀበሌ 11/12 በሚገኘው የካራአሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከግቢ ውጭ በአግባቡ ያልተወገደ መርፌ አግኝተው እርስ በእርስ በመወጋጋታቸው ጉዳት አድርሷል።

ጉዳዩ የተከሰተው ጥር 8 እና 9 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሆነና ተማሪዎች እርስ በእርስ በመወጋጋታቸው ጉዳት እንደረሰባቸው የቀጠናው ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስና የወረዳ 12 የሜዲካል ዳይሬክተር ገልጸዋል። 

የየካ ክፍለ ከተማ የኮተቤ ፖሊስ ጣቢያ የረድኤት ቀጠና የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ኦፊሰር ሳጅን ምስክር አርአያ የመርፌው መገኛ በተመለከተ ፖሊስ ማጣራት እንዳደረገ ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎችም የማነጋገር ስራ እንደተከናወነና መርፌው የስኳር ህመምተኞች የስኳር መጠናቸውን ለመለካት የሚጠቀሙበት መርፌ በመሆኑ ግለሰቦች ሊጥሉት ይችላሉ የሚል ግምታዊ አስተያየት እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

በቦታው የተገኙ መርፌዎች እንዲወገዱ እንደተደረገና ወደ ማህበረሰቡም በመውረድ የማረጋጋት ስራም እንደተሰራ ጠቅሰዋል።

በግለሰብ ወይስ በተቋም ደረጃ መርፌው ተጣለ? የሚለውን ጉዳይ ላይ አሁንም ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና በቸልተኝነት ይሄን መርፌ የጣለው አካል ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጥ ገልጸዋል።

መርፌውን ያመጡት ልጆች የ9 እና የ11 ዓመት እድሜ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በክፍለ ከተማው የወረዳ 12 ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ግርማ መርፌው በአግባቡ ባለመወገዱ ምክንያት ተማሪዎቹ እንደተጎዱና ስለታማው ነገር አገልግሎት ላይ ከዋለ በኋላ በፍጥነት መወገድ እንደበረበት ይናገራሉ።

ስለ ጉዳዩ መረጃ የደረሰው ጤና ጣቢያው በፍጥነት የህክምና ቡድን በመላክ ተማሪዎች ወደ ህክምና ጣቢያው እንዲመጡ በማድረግ አስፈላጊ ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረው፤ ህብረተሰቡ በተለያዩ ቦታዎች የህክምና ቁሳቁሶች ተጥሎ ሲያገኝ ለሚመለከተው አካል በፍጥነት ማሳወቅ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ህጻናቶቹ የቲታነስና የጸረ-ኤችአይቪ/ኤድስና የቲታነስ መድሃኒት እንደተሰጣቸው ገልጸው ደሙ መርፌው ላይ ቆይቶ ኤችአይቪ/ኤድስ ልጆቹ የመያዛቸው ዕድል 0.03 በመቶ እንደሆነም አስረድተዋል።

ህጻናቶቹ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

በመርፌ ተወግተው ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ወላጆች ትምህርት ቤቱ በተማሪዎቹ ላይ ጉዳት እንደደረሰ ቶሎ አለማሳወቁ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ኢዜአ በትምህር ቤቱ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የተማሪዎቹ ወላጆች “ተማሪዎቹ በመርፌው ተወግተው ጉዳት ሲደርስባቸው ትምህርት ቤቱ ስለጉዳዩ በፍጥነት ለወላጆች አለመንገሩ ተገቢነት የለውም” ይላሉ።

አቶ ዳኜ ፈለቀ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ የዘጠኝ ዓመት ልጃቸው አንገቱ ላይ በመርፌ ተወግቶ ጉዳት እንደረሰበትና ራሱን ስቶ ወድቆ ተማሪዎች ወደ ቤቱ ይዘውት እንደመጡ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ በኩል በጉዳዩ ዙሪያ ወላጆች የሚፈልጉትን መረጃ እየሰጠ እንዳልሆነና መረጃም እንዲሰጡ ሲጠይቁ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

ሌላኛዋ ወላጅ አልማዝ ንጉሴ ስለተከሰተው ጉዳይ ትምህርት ቤቱ ቶሎ አለማሳወቁ በፍጥነት መፍትሄ እንዳይሰጥ እንዳደረገ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ ጉዳዩን ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን አጣርቶ ስለ ጉዳዩ ግልጽ መረጃ ለወላጆቹ መስጠት እንዳለበትና ይሄ ነገር በትምህርት ቤቱም ሆነ በሌላ ትምህርት ቤት ዳግም እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ መደረግ እንዳለበት ጠቁማለች።

የካራአሎ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አዲስ አለማየሁ ተማሪዎቹ በመርፌው እንደተወጉ መረጃው የደረሳቸው ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም መሆኑን ገልጸው አስፈላጊውን ድጋፍ በፍጥነት እንዲደረግ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ለፖሊስ ጉዳዩን በማሳወቅ መርፌውን ያመጣው ተማሪ መርፌውን ከየት እንዳመጣው ለፖሊሶች ሄዶ እንዲያሳያቸው መደረጉንና መርፌውን የተገኘው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 መድሐኒያለም ቤተርክርስቲያን አጠገብ የሚገኝ ጫካ ውስጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመርፌ የተወጉት 68 ተማሪዎች የህክምና እርዳታ እንደተረገላቸውም አክለዋል።

በትምህርት ቤቱ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉት የጥበቃ ሰራተኞች ዘጠኝ ብቻ በመሆናቸው 2 ሺህ 638 ተማሪዎችን መጠበቅ አዳጋች እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ትምህርት ቤቱ የወላጆችን ስጋት እንደሚረዳና ችግሩን ለመፍታት አስላጊውን ጥረት ማድረጉን ገልጸው ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት እንዲልኩ ጠይቀዋል።