ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በመሳተፍ ላይ ናችው

47

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው የልኡካን ቡድን የጣሊያን ቆይታውን አጠናቆ ስዊዘርላንድ ዳቮስ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም  እየተሳተፉ ነው።

የልኡካን ቡድኑ በጣሊያን በነበረው ቆይታ ከአገሪቷ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይቶችን ማካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ  የተመራው የልኡካን ቡድኑ ከጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ እና ከጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፕ ኮንቴ ጋር አገራቱ በሁሉም ዘርፍ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በሚቀጥሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክራው ከስምምነት ደርሰዋል።

የጣሊያን መንግስት በኢትዮጵያ የሚሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶቸን በገንዘብ ለመደገፍ ቃል መግባቱንም መሪዎቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጠዋል።

የጣሊያን መንግስት ከአዲስ አበባ ምጽዋ ለሚገነባው የባቡር ሃዲድ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ጥናት ሙሉ ወጪውን ለመሸፈንም ቃል መግባቱ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምግባ ለማካሄድ የሚያግዝ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ /የዳቦ ፋብሪካ/ ለመገንባትም ቃል መግባታቸውንና ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ምስጋና ማቅረባቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ፣ ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ድ ሲልቫ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሬዝዳንት ሮበርት ጊልበርት ጋርም ድርጅቶቹ የልማት አጋርነታቸውን አጠናክረው በሚቀጥሉበት ጉዳይ ዙሪያ ተነጋግረዋል።

በተጨማሪም ከሮማው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፍራንሲስ ጋር፣ በቫቲካን የቅዱስ እስጢፋኖስ የአቢሲኒያ ቤተክርስቲያን ከካርዲናል አባ ብርሃነየሱስ ጋር እንዲሁም ከቫቲካን ዋና አስተዳዳሪ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጋርም ተወያይተዋል።

በዚህም አገራቱ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በመጠቀም የህዝብ ለህዝብ እና የባህል ትስስሩን አጠናክረው መቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወቅርነህ ገበየሁ በበኩላቸው የጣሊያን ታዋቂ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በተዘጋጀው ፎረም ላይ በመገኘት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

ባለሀብቶቹም በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶችም ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በተመለከተ ያላቸውን ተሞክሮና ምስክርነት ሰጥተዋል።

በስዊዘርላንድ ዳቮስ የሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ

ፎረም ''መፃዒ እድላችንን በጋራ እንወሰን'' በሚል መሪ ቃል በርካታ የዓለም መሪዎችን ጨምሮ፣ የዓለም አቀፍ ካምፓኒ መስራቾችና ባለሀብቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የሙያው ጠበብቶች እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች በአጠቃላይ ከ3000 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት በዛሬው እለት በይፋ ተከፍቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፎረሙ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም