ጀርመን በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ እውን እንዲሆን ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች

43
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚስትር ሄይኮ ማስ ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ጋር በኢትዮጵያና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያዩ። ኢትዮጵያ በሰላማዊ ሽግግር አዲስ የአመራር ለውጥ ማድረጓን ተከትሎ በአገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት እንደመጡ ነው የተገለፀው። ሚኒስትር ደኤታዋ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለፃ አድርገውላቸዋል። አገሪቱ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማድረጓንና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለውጥ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብዙ ክልከላ የሌለበትና ኢንቨስተሮች በተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ያስቻለ እንደሆነም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም አስከባሪ ከመላክ ጀምሮ የቀጠናውን ሰላም ለማረጋጋት የበኩሏን እየተወጣች እንደሆነ አብራርተዋል። የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በማድነቅ ለለውጡ ሂደት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ለቀጠናው ሰላም ጠንክራ እንድትሰራ ጀርመን የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል። የጀርመን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ታዳሽ ሀይል ኢንቨስትመንት የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ከውይይቱ በኋላ ኢትዮጵያ የኢጋድ ሊቀመንበር እንደመሆኗ በተለይም በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት በመረዳት የመደገፍ ዕቅድ መኖሩን ተናግረዋል። ጀርመን በአውሮፓ ህብረት አገሮች ተፅእኖ ፈጣሪ በመሆኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሚስተር ሃይክ ማስ ከስድስት ወር በፊት የተሾሙ ሲሆን በአፍሪካ  ጉብኝት ሲያደርጉ የኢትዮጵያው የመየመጀመሪያ ጉብኝታቸው ነው፡፡  ታንዛንያንም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም