በበጋ ወራት የአካባቢ ጥበቃ 263 ሺህ ሄክታር መሬት እየለማነው

61

ነቀምቴ/ መቱ ጥር 14/2011 በምሥራቅ ወለጋና በኢሉአባቦር ዞኖች 263 ሺህ ሄክታር መሬት በሚያለሙ 527 ተፋሰሶች ላይ የበጋ ወራት የአካባቢ ጥበቃ ልማት ሥራዎች ዛሬ ተጀመሩ ።

”መሬታችን አጥንታችን ነው” በሚል መርህ ዛሬ በምስራቅ ወለጋ ዞን የተጀመረው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ 132 ሺህ ሔክታር መሬት በሚያለሙ 265 ተፋሰሶች ላይ የሚካሄድ ነው።

ለአንድ ወር በሚቆየው ሥራ 208 ሺህ 890 አርሶአደሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣27 ሺህ 299 ሄክታር መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ይደረጋል ።

የኦሮሚያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በአካባቢው የፀጥታ ችግር ቢኖርም፤ሕዝቡ መሬቱን ከጉዳት ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ስራው በዞን ደረጃ በዲጋ ወረዳ በወዬሣ ዲምቱ ቀበሌ በይፋ የተጀመረው የአገር ሽማግሌዎች፣አርሶ አደሮች፣ሴቶች ፣መምህራን፣ተማሪዎች ፣የወረዳ፣የዞንና የክልል አመራሮች በተገኙበት ነው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በኢሉአባቦር ዞን የተጀመረው የአካባቢ ጥበቃ ልማት ሥራ በ262 ተፋሰሶች 131 ሺህ ሔክታር መሬት ለማልማት ያለመ ነው

የኢሉአባቦር ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ለገሰ እንደገለጹት በዞኑ 13 ወረዳዎች ለሶስት ወራት በሚቆየው ሥራ ከ190 ሺህ በላይ አርሶአደሮች ይሳተፋሉ፡፡

15 ሺህ 822 ሄክታር መሬት ደግሞ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ተደርጎ ይከለላል።

የአሌ ወረዳ ድልዲላ ቦሩ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አህመድ ፋሪስ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ባከናወኑት የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈር መሸርሸርን በመቀነሱ  ከዚህ ቀደም ከልማት የወጡ አካባቢዎች መልሰው መልማት ጀምረዋል፡፡

“ወደ ሜዳማነት ተቀይሮ የነበረው ሁለት ጥማድ ማሳ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በቆሎ እያለማሁበት ነው” ያሉት አርሶአደሩ፣ ይህም በልማቱ ለመሳተፍ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንደጨመረላቸው ገልጸዋል፡፡

በኢሉ አባቦር ዞን ባለፉት አምስት ዓመታት ከ326 ሺህ 763 ሄክታር  መሬት ላይ አርሶአደሩን ያሳተፈ የተፋሰስ ልማት ሥራ ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም