“የእድል መስኮት !”

159

መሐመድ ረሻድ ጎባ ኢዜአ !

እለቱ ሰንበት ነው፡፡ የአየሩ ሁኔታም ብዙም ጥሩ ስላልነበር ከመኝታዬ ዘግይቼ ነበር የተነሳሁት፡፡ ዘወትር ማልዶ ይቀሰቅሰኝ የነበረው የጎረቤቶቼ የነወይዘሮ አለምፀሃይ ታደሰ ድምፅ ዛሬ ጭር ብሏል፡፡

ስለሁኔታው ሳጣራ ሌሊት ምጥ ይዟት ወደ ሆስፒታል መሄዷ ተነገረኝ ፡፡ እኔም ከመደበኛ ስራዬ በፊት ማህበራዊ ኃላፊነነቴን ለመወጣት ወደ ሆስፒታል አቀናሁኝ ። በወጋችንና በባህላችን  መሰረት ” እንኳን ማሪያም ማረችሽ!” ማለቱን አስቀደምኩኝ ።

ወይዘሮ ዓለምፀሃይ በሰላም ተገላግላለች ። ባለቤቷ አቶ ግርማ ገመቹ በደስታ ብዛት ፊቱ እያበራ አጠገቧ ቆሟል ።

አዲሱን ዓለም የተቀላቀለው ህፃን በጤና ባለሙያዎች አነጋገር እንደ መጀመሪያ ክትባት የሚቆጠረውን እንገር የእናቱን ጡት ያለማንም ከልካይ እየጠባ ይታያል፡፡ አጠገባቸው ሆና  የህክምና እርዳታ እያደረገችላቸው የምትገኘው ነርስ እንደነገረችኝ የነወይዘሮ አለምፀሃይ ደስታን እጥፍ ድርብ ያደረገው ከጽንስ ወቅት ጀምሮ ተከታታይ የቅድመ ወሊድ የእርግዝና ክትትል ማድረጋቸውና በጤና ተቋም በጤና ባለሙያ መገላገሏ መሆኑን ትናገራለች፡፡

 ለነገሩ እኔም ጎረቤቶቼ ለቅድመ ወሊድ ክትትል ወደ ሆስፒታል ሲመላለሱ ብዙ ጊዜ ተመልክቼያለሁና  ምስክር ነኝ፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነቴን ከተወጣሁኝ በኃላ ተሰናብቻቸው ወደ ቤቴ ለመሄድ ተቻኩዬ ወጣሁኝ፡፡ እነ ወይዘሮ አለምፀሃይ የተኙበት ክፍል አጠገብ  በከፍተኛ የህክምና ክትትል ስር የሚገኙ ህፃናት ክፍል የሚል ጽሁፍ አነበብኩኝ፡፡

ከውስጥ የሚያለቅሱ ህጻናት ድምጽ ተሰማኝ ፡፡ ወደ ክፍሉ ገብቼ ለመጎብኘትም ወደድኩኝና ወደ ውስጥ ስዘልቅ እንግዳ ነገር አስተዋልኩኝ ፡፡ መደዳውን የተኙት ሶስት ህፃናት የእናታቸውን ጡት እየጠቡ አልነበረም ፡፡ ይልቁንም ከተለምዶ የተፈጥሮ የምግብ አወሳሰድ በተፃራሪ በአፍንጫቸው በኩል በፕላስቲክ ቱቦ ምግብ ሲሰጣቸው እንጂ፡፡

መጠየቅ የስራ ባህሪያችን አንዱ አካል አይደል ? መደዳውን ህፃናትን ታቅፈው ከተቀመጡ እናቶች መካከል ወደ አንዷ ጠጋ ብዬ ማነጋገር ጀመርኩኝ ፡፡ ወይዘሮ ሀምዚያ በከር ይባላሉ፡፡ ከዞኑ ዳዌ ቃቸን የአርብቶ አደር ወረዳ ለህፃናቸው የተሻለ ህክምና ሪፈር ተብለው ወደ ሆሰፒታሉ እንደመጡ ነገሩኝ፡፡

እናቶቹ ህፃናቱ ምን እንደታመሙ ራሱ በውል የተረዱ አይመስሉም ፡፡ ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘ በሽታ እንደሆነ በጤና ባለሙያዎች እንደተናገራቸውና ውጤቱም ከመጡበት ወቅት የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከእናቶች ጋር በነበረኝ ቆይታ የተወሰነ ነገር ባገኝም መርካት አልቻልኩም፡፡ በሪፈራል ሆስፒታሉ በህፃናት ህክምና የሚታወቁትን ዶክተር ተከተል ጥላሁንን በስልክ አገኘኋቸው፡፡

በሆስፒሉ ውስጥ ተኝተው የሚታከሙ ህሙማን ያሉበትን ሁኔታ ጎብኝተው ካጠናቀቁ በኋላ ተገናኘንና ተያይዘን በህፃናት ክፍል የታዘብኩትን እንግዳ ነገር እንዲያብራሩልኝ ወደዚያው አቀናን፡፡

ዶክተሩ ሚስጢሩን እያፍታቱ መናገር ጀመሩ፡፡ የህፃናቶቹ ችግር ከምግብ እጥረት “malnutrition” የሚመጣ በሽታ ነው ብለው ጀመሩ ። እናቶች በማህጸናቸው ፅንስ መያዝ ከጀመሩበት እለት አንስተው ለፅንሱ የሚያደርጉት እንክብካቤ ከራሳቸውም ጤና አልፎ በህፃናት የነገ ተሰፋ ላይ አሉታዊና አዎንታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው አብራሩልኝ፡፡

 ሀገራችን ኢትዮጵያም በ2035 የምግብ እጥረትን ጨምሮ የህፃናት ገዳይ የሆኑ ተላላፊ በሽታዎችንና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሚወለዱ አንድ ሺህ ህፃናት መካከል የሚሞቱትን የህፃናት ቁጥር ከ20 በታች ለማውረድ ግብ ጥላ እየሰራች እንደምትገኝ ዶክተር ተከተል አብራሩልኝ ፡፡

ነገርን ነገር ያነሰዋል እንደሚሉት በሆስፒታሉ የገጠመኝ እንግዳ ነገር በቅርቡ በአዳማ ከተማ የታደምኩበትን በስነ-ምግብ “nutrition” ላይ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተዘጋጀው ዓውደጥናት የነበረውን ዋነኛ አጀንዳ አስታወሰኝ ።

ፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ  የተባለ ተቋም  የኦሮሚያ ፕሮጄክት አስተባባሪ ወይዘሮ እትመልሻ መሸሻ እንደተናገሩት ተቋማቸው በዋናነት በእናቶችና ህፃናት የስነ ምግብን ጨምሮ በሌሎች የትኩረት መስኮች ላይ በአገሪቱ 43 ወረዳዎች ውስጥ እየሰሩ ነው ።50 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ በኦሮሚያ ውስጥ ነው ።

በአሜሪካን ህዝብ ድጋፍ “USAID” የሚካሄደው ይህ ፕሮጄክት አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የሚያመርተውን ሰብል ለምግብ ግብዓትነት እንዲጠቀም ብሎም የተረፈውን ለአካባቢው፤ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ራሱን እንዲያዳብር ማድረግም ከፕሮጄክቱ ዓላማዎች መካካል ይጠቀሳል ፡፡ 

 በዚሁ ተቋም የስነ ምግብ ምንነት፤ አይነትና ፈተናዎቹን የሚዳስስ ስልጠና ተዘጋጅቶ ነበር ።የስልጠናውን ጽሁፍ ያቀረቡት የስነ ምግብ አስተባባሪ አቶ ዘውዱ ጌታቸው ናቸው፡፡ ስነ ምግብ “ በአፋችን በኩል ወደ ውስጥ የምናስገባው የምግብ አይነት ሆኖ ለሰው ልጆች አካላዊና አእምሮአዊ ግንባታ የሚውል ንጥረ ነገር ያዘለ ነው ሲሉ ይገልፁታል ።

ለሰው ልጆች ጤናማ ህይወት የአመጋገብ ስርዓቱን ጤናማ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣው ተግባር መሆኑን ያስረዳሉ ፡፡ ጤናማ የአመጋጋብ ስርዓት የሚባለው “የተመጣጣነ ምግብ ”Balanced diet” መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

 የስነ ምግብ ጠበብቶች እንደሚሉት አንድ ምግብ የተመጣጣነ ምግብ  ነው ብሎ ለመፈረጅ ማሟላት የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ ። አንድ ሰው የተመጣጠነ ምግብ ተመግቧል የሚባለው በቀን ውስጥ በትንሹ አራት የተለያዩ ዓይነቶችን ቀላቅሎ ሲመገብ ነው ።

የተመጣጠነ ምግብ በአካባቢያችን ከምናመርታቸውና በቀላሉ በገበያ ላይ ከምናገኛቸው ምግቦች  መካከል አቅማችንን መሰረት በማድረግ በቤታችን ውስጥ ማዘጋጀት ይቻላል ይላሉ፡፡

ማድረግ እየቻልን  ባለማድረጋችን በምግብ እጥረት ምክንያት  ለሚመጣው “malnutrition “  በሽታ የመጋለጥ እድሉ ሰፊ ይሆናል ነው የተባለው፡፡  በህፃናት ላይ የሚታየው መቀንጨርም ከዚሁ ጋር የተያየያዘ ነው ።

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በህፃናት ላይ የሚታየው የምግብ እጥረት ተጋላጭነት እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ድረስ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት ህፃናት መካከል  38 በመቶ የሚሆኑት ለዚሁ ችግር ተጋላጭ በመሆናቸው ቀጣዩ  ስራ ከባድ ያደርገዋል ።

 በተለይ 22 በመቶ የሚሆኑ በመውለድ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እናቶች በምግብ እጥረት በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱም ተናግረዋል፡፡

እነዚህ እናቶች የሚወልዷዋቸው ህፃናትም ከዕድሜያቸው አንፃር ሲታይ ያላቸው ክብደትና ርዝመት ተመጣጣኝ ካለመሆኑ የተነሳ የበሽታ ተጋላጭነታቸው እየጨመረ እንደሚመጣ ይናገራሉ፡፡

ችግሩ የሚፈታው ህፃናት ከተጸነሱበት ጊዜ አንስቶ በእናታቸው አማካኝነት ጤናማ ምግብ እንዲደርሳቸው በማድረግ ፣ ተወልደው 6 ወራት እስኪሞላቸው ድረስ የእናት ጡት ብቻ እንዲጠቀሙና ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ደግሞ ከተጨማሪ ምግብ ጋር ማጥባቱን ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ነው ። ሒደቱም 1ሺህ ቀናትን ይፈጃል ማለት ነው ።

ይህ ሒደት በዘርፉ ባለሙያዎች አንደበት የእድል መስኮት ! ወይም "አንድ ሺህ የህይወት ቀናት !" ተብሎ ይጠራል ። ምክንያቱ ደግሞ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚደረገው እንክብካቤ የህፃናትን አካላዊና አእምሮአዊ እድገት ደረጃ የሚወሰንበትና “የእድገት እርከን ወሰን” የሚገደብበት ወቅት በመሆኑ ።

 በምግብ እጥረት ምክንያት የሚመጣው በሽታ የህፃናት የተፈጥሮ የመከላከልና የአስተሳሰብ አድማሳቸውንም ጭምር የማጥበብ አሉታዊ ተጽእኖም አለው ይሉታል፡፡

እነዚህ አንድ ሺህ የህይወት ቀናት የህፃናትን የወደፊት እጣ ፈንታ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ተጽእኖ የሚያደርጉ “የእድል መስኮት” critical window opimal growth” በመባል እንደሚታወቁም አቶ ዘውዱ  ያስረዳሉ፡፡

ምክንያቱም  በምግብ እጥረት ሳቢያ የሚመጡ የመቀንጨር በሽታዎች በቀጣይ ለህፃናት በሚደረጉ እንክብካቤዎች በተወሰነ መልኩ አካላዊ ለውጥ ማምጣት ይቻል ይሆናል ። አእምሮአዊ እድገቱን ማስፋት የሚቻለው ግን ህፃኑ ከተፀነሰበት እለት ጀምሮ ተወልዶ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ባሉት 1ሺህ ቀናት ውስጥ በሚደረግለት እንክብካቤ ልክ ብቻ የሚወሰን በመሆኑ ነው  ።

ምንም እንኳ ሀገራችን በስነ ምግብ ዘርፍ ላይ እስከ አሁን የፀደቀ ፖሊሲ ባይኖራትም የችግሩን አሳሳቢነትና ጥልቀት በመረዳት የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ጨምሮ በሌሎች ብሔራዊ የስነ ምግብ ስትራቴጂና ኢንሼቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች፡፡ የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ የሚባለውም ሆድ መሙላት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ ህፃናት የተመጣጣነ ምግብ ሲያገኙ ነው ።

በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረገው ኮስት ኦፍ ሀንገር የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ያካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ በዓመት ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ 50 ቢሊዮን ብር ታጣለች ፡፡

ይህ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያሳያል፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎችም ለህፃናት ጥብቅና በመቆምና ችግሩ እንዲፈታ የበኩላቸውን እገዛ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ።  የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን እጣ ፋንታ በመወሰን በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው የስነ ምግብ ጉዳይ  ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም የበኩላችን ድርሻ እንወጣ እንላለን፡፡ ጤና ይስጥልኝ !

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም