የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ ሳይጀመር ከሦስት ዓመት በላይ በመቆየቱ ቅሬታ አስነሳ

89

ደብረብርሀን ጥር 14/2011  በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጎለላና ጠራ ወረዳ የአጅማ ጫጫ ከፍተኛ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ከሦስት ዓመት በላይ ሳይጀመር መቆየቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለፁ።

በአጎለላና ጠራ ወረዳ ቡራና ጦጦሴ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ደረጀ ገዙ ለኢዜአ እንደገለጹት የፕሮጀክቱ መሰረት ድንጋይ ሲጣል የሥራ እድል ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ተስፋ አሳድሮባቸው ነበር።

ግንባታው ሲጠናቀቅም በዘመናዊ መስኖ ተሰታፊ በመሆን የተሸላ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው ቢጠብቁም እስካሁን የግድቡ ግንባታ አለመጀመሩ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደር ለጠጠር ማምረቻና ለሠራተኞች ማደሪያ ካምፕ ግንባታ የሚውል መሬት ማቅረቡን አስታውሰው እስካሁን የመስኖ ግንባታው አለመጀመሩ በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን አስታውቀዋል።

ለፕሮጀክቱ ግንባታ የእርሻ መሬታቸውን ቢሰጡም እስካሁን ድረስ ለእርሳቸውም ሆነ ለሌሎች አርሶ አደሮች ካሳ ባለመከፈሉ መቸገራቸውን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ምንድሽ ፀጋ ናቸው።

አካባቢው ደጋማ በመሆኑ የመኽር ሰብላቸው በተደጋጋሚ በውርጭ እየተጠቃ ምርታማነቱ እየቀነሰ መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሩ የመስኖ ፕሮጀክቱ በተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ተስፋ አሳድሮባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ከመሬቱ ያገኙት የነበረውን የሦስት ዓመት ሰብል ከማጣታቸውም በላይ ሥራው ባለመጀመሩ በአሁኑ ወቅት በመስኖ ልማቱ ተሳታፊ በመሆን ለመጠቀም የነበራቸው ተስፋ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሚመለከተው የመንግስት አካል የፕሮጀክቱ ግንባታ በአፋጣኝ የሚጀመርበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቀዋል።

የዞኑ ውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ምንሽር በበኩላቸው እንዳሉት የአጅማ ጫጫ ግድብ ከፍተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ የክልሉ መንግስት በመደበው 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚከናወን ነው።

የመስኖ ግንባታው የመሰረት ድንጋይ በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ሲቀመጥ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ቢባልም ግንባታው ሳይጀመር ሦስት ዓመት እንደሞላው ተናግረዋል።

የዲዛይን ሥራው እንደገና መሻሻሉና ከመሬታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮች በወቅቱ ካሳ አለመከፈል ግንባታው እንዳይጀመር ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ለመስኖ ፕሮጀክቱ የእርሻ መሬታቸው ለተወሰደባቸው 577 አርሶ አደሮች ካሳ ለመክፈል የልየታና የግመታ ሥራ ተጠናቆ ካሳ መስጠት መጀመሩንም አመልክተዋል።

አቶ ኤፍሬም እንዳሉት የግድቡ ግንባታ ሥራ ባይጀመርም ወደ ፕሮጀክቱ የሚያስኬድ የመንገድ ሥራ፣ የሠራተኞች ማደሪያ ካፕ ግንባታ እንዲሁም የንጹህ የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከግድቡ የሚተርፈው ውሃ የሚፈስበት ቦይ ግንባታ ሥራን በዚህ ዓመት ለማስጀመር የክልሉ መንግስት 100 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

"የዋናው ግድብ የግንባታ ሥራም በዚህ ዓመት ሥራ ይጀመራል" ሲሉም አመልክተዋል።

በአጅማ ወንዝ የሚገነበው ዘመናዊ የመስኖ ግድብ 639 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን ግንባታው በቀጣይ አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ልማት ሲገባ 7 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚያስችል አቶ ኤፍሬም አስታውቀዋል።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ በ10 ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም