የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ተደራሽነት በቂ አይደለም...የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

57

አዳማ ጥር 13/2011 የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ተደራሽነት በቂ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርጎ ያካሄደውን ጥናት ከባለድርሻ አላት ጋር በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ተደራሽነት ክፍተት እንዳለበት በጥናት ተረጋግጧል።

ተቋማቱ ለአካል ጉዳተኞው ያላቸው ተደራሽነት ችግሮችን ለመለየት አዲስ አበባና ድሬ ዳዋ ከተሞችን ጨምሮ በ11 ዋና ዋና የክልል ከተሞች ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል።

በጥናቱም የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከግንባታ፣ ከአደረጃጀትና አሰራር አኳያ አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ አለማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ዶክተር አዲሱ እንዳሉት ጥናቱ የአካል ጉዳተኞች የሰብዓዊ መብት፣ በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት አሰራርና አደረጃጀት፣ ፖሊስና የህግ ማዕቀፎችን በማስፈፀም በኩል የተለዩ ክፍቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመዋል።

የጥናቱ ዓላማ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ተደራሽነትና ችግሮችን መለየት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በዘርፉ ለሚነሱ ጥያቄዎች የመፍትሄ አቅጣጫና ሀሳብ ለህግ አውጭ አካል በማቅረብ ህግ መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር ለማስቻል መሆኑንም አስገንዝበዋል።

እንደ ዶክተር አዲሱ ገለጻ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን መሰረት አድርገው እንዲተገበሩ የሚያስገድዱ የህግ ማዕቀፎች እንዲወጡ ለማድረግ ጭምር ታስቦ ጥናቱ መካሄዱን አስታውቀዋል።

በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በኮሚሽኑ የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት የጥናት ባለሙያ ወይዘሮ ሰላሚዊት አወቀ በበኩላቸው የግልና የመንግስት የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች አመች ባለመሆናቸው ቅሬታዎች እየተነሱ ነው።

በሀገሪቷ ካሉት የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለአካል ጉዳተኞች አመችና ተደራሽ እንዳልሆኑ በጥናት መለየቱን አመልክተዋል።

የተነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ ጥናቱ በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት፣ በፍትህ፣ በሚዲያ ተቋማት፣ በመዝናኛ ማዕከላት፣ በህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን አስታውቀዋል።

መድረኩም በጥናቱ ግኝት ላይ ከባለድርሻ አካላት ግብዓት ለማሰባሰብና ለማዳበር ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ከአካል ጉዳተኞች፣ ከተለያየ የዘርፍ ማህበራትና አደረጃጀቶች፣ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተወጣጡ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም