በፕላዝማ የሚሰጥ የትምህርት አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን በደሴ የሚገኙ ተማሪዎች ገለፁ

52

ደሴ ጥር 13/2011 በደሴ ከተማ አስተዳደር በፕላዝማ የሚሰጥ የትምህርት አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን ተማሪዎች ገለፁ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ በኃይል እጥረት፣ በብልሽት፣ በመለዋወጫ አቅርቦትና በመሳሰሉት ችግሮች ፕላዝማዎቹ ተገቢውን አገልግሎት እንደማይሰጡ አምኗል፡፡

በቦሩ ሥላሴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ተምር ጀማል በትምህርት ቤቱ የፕላዝማ አገልግሎት ባለመኖሩ የተሻለ አደረጃጀት ካላቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጋር ለመወዳደር እንዳስቸገራቸው ገልጻለች፡፡

በተለይ የሂሳብና የፊዚክስ ትምህርት የማጣቀሻ መጻህፍት እጥረት ስላለባቸው የፕላዝማው መኖር እጥረቱን ከማቃለል ባሻገር፤ ተግባራዊ ዕውቀት ለመቅሰም ያግዘን ነበር ብላለች።

በርካታ ተማሪዎች ወዳላቸው ትምህርት ቤት እየተዘዋወሩ መሆናቸውን ትናገራለች።

ከዘጠነኛ ክፍል ሁለተኛ በመውጣት 10ኛ ክፍልን የተቀላቀለው አይመን ይመር በበኩሉ በትምህርት ቤቱ የፕላዝማው አለመኖር ትምህርታቸውን በተገቢው መንገድ ለመከታተል  እንዳላስቻላቸው ይገልጻል።

መንግሥት በተለይ ለሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ከሰጠው ትኩረት አንጻር ፕላዝማዎቹ ያለ አገልግሎት መቀመጣቸው ኪሳራ ነው ብሏል፡፡

የቦሩ ሥላሴ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ፍቅር በላይ እንደሚሉት ለትምህርት ቤቱ ከሶስት ዓመታት በፊት የመጡት 32 ፕላዝማዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት ያለ አገልግሎት ተቀምጠዋል፡፡

የፕላዝማዎቹ አገልግሎት አለመጀመር የመንግሥት ሀብት ጉዳት እንዲደርስበት ከማድረጉ ባለፈ ትምህርት ቤቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የበለጸገና ተወዳዳሪ ተማሪ ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

ችግሩን ለሚመለከተው አካላት በተደጋጋሚ አቅርበው መፍትሄ አለማግኘታቸውን ርዕሰ መምህሩ ያስረዳሉ፡፡

የከተማው አስተዳደር ትምህርት መምሪያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ኡመር አረጋ በከተማ አስተዳደሩ በመንግሥት ከሚተዳደሩት ዘጠኝ የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች መካከል አራቱ ፕላዝማ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡

በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ካሉት 274 ፕላዝማዎች ውስጥ 71ዱ በብልሽት፣ በኃይል አቅርቦትና በመለዋወጫ እጥረትና በኢትዮ ቴሌኮም የሚገጠሙ ሞጂሌተሮች አለመኖር ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት አይሰጡም ብለዋል፡፡

አንዳንዶቹም ተገዝተው ባለመገጠማቸው ለዝገትና ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምስራቅ ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ማስረሻ ገበየሁ በፕላዝማዎቹ ብልሽት ላይ  የደረሳቸው ዝርዝር መረጃ ባለመኖሩ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

ከሞጁሌተር ውጭ ያሉ ጉድለቶችንና ብልሽቶችን የተቋሙ ባለሙያዎች ለማስተካከል ትምህርት ቤቶቹ ፕላዝማዎቹ ያሉበትን ይዞታ የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል፡፡

ከሞጁሌተር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ግን ከቅርንጫፉ አቅም በላይ በመሆናቸው ከውጭ ተገዝተው በማዕከል በኩል ሲደርሳቸው  እንደሚያሰራጩ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡  መቼ;

በአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የአማራ ሪጅን የደሴ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳለ ኪዳኔ በበኩላቸው የቦሩ ስላሴ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ የአካባቢውን ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ2008 አጋማሽ የተጀመረው እንቅስቃሴ በቁሳቁስ አቅርቦት እጥረትና  በአካባቢው መልክዓ ምድር አቀማመጥ አለመመቸት መጓተቱን አመልክተዋል፡፡

ካለፈው ወር ጀምሮ ግን የመስመር ዝርጋታው ተጠናቅቆ በመሥመሩ አካባቢ ያለውን የግለሰቦች ዛፍ እንዲቆረጥና ካሳ እንዲከፈል ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረቡት ማሳሰቢያ ምላሽ ባለማግኘቱ አገልግሎቱን ለመስጠት ችግር ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡     

የከተማው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመቀ ቦሩ የካሳ ክፍያ ጥያቄው በአፋጣኝ ምላሽ ያላገኘው በዋነኝነት በአመራሮች መቀያየርና በአካባቢው በተፈጠረው  አለመረጋጋት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኤሌክትሪክ  ዝርጋታው ከሚከፈለው አንድ ሚሊዮን ብር ያህል ውስጥ አስተዳደሩ 40 በመቶውን እንደሚሸፍንና ቀሪው በሕዝቡ እንደሚሸፈን ተናግረዋል፡፡

ለግለሰቦች የሚከፈል ካሳም ካለ ተጠንቶ እንደቀረበልን ክፍያው ይፈጸማል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም