ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የደም ልገሳን ባህል ማድረግ ያስፈልጋል-- የጤና ሚኒስቴር

100

አዲስ አበባ ጥር 13/2011 ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የደም ልገሳን ባህል ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

''በደም መፍሰስ የሚደርሰውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል'' በሚል መሪ ሃሳብ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረው የእናቶች ወር በተለያየ መልኩ እየተከበረ ነው።

የጤና ሚኒስቴር ሰራተኞች ወሩን በማስመልከት ዛሬ የደም ልገሳ አድርገዋል።

ከሰራተኞች ጋር በመገኘት ደም የለገሱት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሃርላ አብዱላሂ እንደገለጹት፤ በደም እጦት ምክንያት ብዙ ወላድ እናቶች ህይወታቸውን ያጣሉ።   

የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ የሚኒስቴሩ ሰራተኞች አረአያ እንዲሆኑ በዘመቻ የደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።

በደም ልገሳው የተሳተፉት የተቋሙ ሰራተኞች በበኩላቸው፤ የእናቶችንና የህጻናትን ህይወት ለመታደግ እንዲሁም ሞት ለመቀነስ የደም ልገሳ  እየተደረገ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

በመሆኑም የበጎ ፍቃድ ደም ለጋሽ ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድና የደም አቅርቦት ችግር እንዳይኖር ክልሎችና ሆስፒታሎች  በተቀናጀ መልኩ ተቀራርበውና ህብረተሰቡን አስተባብረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር ዶክተር  ተገኔ ረጋሳ  የሚሰማኝ ደስታ  ብዙ ነው ደሙም የሚተካ ነው ወሩም የእናትነት ስለሆነም እናቶች ወይ ደም በመፍሰስ ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ እነዛን እናቶች ለመታደግ በጣም ደስታ ነው የሚሰማኝ ደም በመለገስ በኩል ትንሽ ግንዛቤው እየተስተካከለ መጥቷል በተለየ የእናቶችንና የህጻናትን ህይወት ለመታደግ፤ ሞት ለመቀነስ ደም በመለገስ  በየወቅቱ የተለያዩ ስራዎች አየተሰሩ ነው ማለት ይቻላል ግን እንዳጠቃላይ ስናይ በቂ አይደለም  ደም በፈቃደኝነት መለገስ አለበት ብለዋል፡፡

የሚኒስቴሩ የበጎ አድራጎት ማህበር አስተባባሪ አቶ ያዕቆብ ወንዲይራድ ደም ልገሳ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው በዓመት ውስጥ ሶስትና አራት ጊዜ ደም እንዲለግሱ ለማድረግ ሚኒስቴሩ እንደሚሰራ ገልጸው እናቶችን ከአደጋ የመጠበቅ ሃላፊነት የሁሉም እንደሆነ ተናግረዋል።

ደም በመለገሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት የሚኒስቴሩ የሪፎርምና መልካም አስተዳዳር ዳሬክተር አቶ አሰፋ አይዴ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የደም እጥረት በመኖሩ በበጎ ፈቃደኝነት ደም የመለገስ ባህሉን ለማሳደግ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ በቤት ውስጥ የሚወልዱና በተለያዩ የመዘግየት ምክንያቶች ወደ ጤና ተቋም የማይሄዱ እናቶች ቁጥር 72 በመቶ የሚደርስ ሲሆን በየዓመቱ ከ100ሺ እናቶች መካከል 412 የሚሆኑት የወለዷቸውን ልጆች ሳያዩ እንደሚያሸልቡ ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም