የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ ሰብዓ እንደርታ እግር ኳስ ክለብ በመቐለ ከተማ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

62

አዲስ አበባ ጥር 13/2011 የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ ሰብዓ እንደርታ እግር ኳስ ክለብ  ዛሬ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

ክለቦቹ ነገ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ ቡናና መቐለ ሰብዓ እንደርታ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ላይ በደጋፊዎቻቸው መካከል ረብሻ መፈጠሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ አመራርና የደጋፊ ማህበር ተወካዮች ከትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አመራሮች እና ከክለቡ ደጋፊ ማህበር ተወካዮች ጋር በመቐለ ከተማ ዛሬ በዚሁ ረብሻና መፈትሄዎቹ ላይ ያተኮረ  ውይይት አካሂደዋል።

የተከሰተውን ችግር በማጣራት መፍትሔ እየተሰጠ እንዲካሄድበት እንዲሁም የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ለእግር ኳስ ስፖርቱ ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባቸው በውይይቱ ላይ መነሳቱን የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለኢዜአ ገልጿል።

በተጨማሪም ሁለቱ ክለቦች ችግሩን ብቻ ከመዘመር በይቅርታ ወደ ሰላማዊው መንገድ በመጓዝ ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዘርፉ ትልቅ ችግር የሆነውን የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ትኩረት በመስጠት በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት እንዲቻል ከሚመለከታቸው አካላት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም