የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እራሳቸውን ለመቻል እየረዳቸው መሆኑን በመቀሌ ተጠቃሚዎች ገለፁ

73

መቀሌ ጥር 13/2011 የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከጊዚያዊ ተጠቃሚነት ባለፈ እራሳቸውን ለመቻል እየረዳቸው መሆኑን የመቀሌ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

ፕሮግራሙ  ከራሳቸው አልፎ  አካባቢያቸውን የማልማት እድል እንደሰጣቸው ነው ተጠቃሚዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተናገሩት፡፡ 

ከተጠቃሚዎቹ መካከል ወይዘሮ ፅጌ ወልደ ሊባኖስ  እንዳሉት በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከታቀፉ ወዲህ  የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅና የዛፍ ችግኞችን በማልማት ውጤታማ ስራ አከናውነዋል፡፡

እሳቸውና ጓደኞቻቸውን ባከናወኗቸው  ስራዎች ከተማው  ጽዱና ውብ እንዲሆን ማስቻላቸው  ገልጸው ሰርተው  ራሳቸውን ለመቻል  ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ታቅፈው በመንቀሳቀስ  አከባቢያቸውን እያለሙ ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ  ወደ ሌላ ስራ ለመሸጋገር እየረዳቸው መሆኑን  ወይዘሮ ፅጌ አስረድተዋል።

“አሁን በኑሯችን ብዙ ተጠቃሚ ባያደርገንም ለቀጣይ ግን ተደራጅተን ለመስራት የቆጠብነው መንግስት ከሚያደርግልን ድጋፍ ጋር ተጨምሮ ቀጣይ ህይወታችን ለመቀየር ተስፋ አድርገናል።”ብለዋል፡፡

በከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም መታቀፋቸው ከራሳቸው አልፎ ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው  የፕሮግራሙ ተጠቃሚ አቶ ወልደገብርኤል  ገብረህይወት  ናቸው።

የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅን ፣አነስተኛና  የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ትርሃስ አብርሃ በበኩላቸው በከተማው በ2009 ዓ.ም የተጀመረው ፕሮግራሙ በየዓመቱ  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን  በማቀፍ ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ኃላፊዋ እንዳሉት የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎቹ በተሰማሩበት የከተማው ጽዳትና ውበት ውጤታማ ስራ አከናውነዋል፤ ከጊዚያዊ ተጠቃሚነት ባለፈ እራሳቸውን ለመቻል  እየረዳቸው ነው፡፡

ተጠቃሚዎቹ በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ስራ ለማከናወን በፕሮግራሙ  ከታቀፉ 8ሺህ 400 ሰዎች ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶ በመቆጠብ አሁን ላይ  ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ማስቀመጣቸውን አስታውቀዋል።

" ከተጠቃሚዎቹ መካከል 2ሺህ ያህሉ በመጪው የካቲት ወር ይመረቃሉ " ያሉት ኃላፊዋ፣ የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።

ስልጠናው የሚሰጠው ተጠቃሚዎቹ በቆጠቡት መሰረት በዘላቂነት የሚቋቋሙባቸው የከተማ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ ፣ አገልግሎት ፣ ግንባታና  ንግድ  የስራ ዘርፎች  መርጠው እንዲሰማሩ ለማስቻል ነው፡፡

ተጠቃሚዎቹ ከማሰልጠን ባለፈ ወደ ስራ የሚሰማሩበት ቦታና የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑት 11 ከተሞች መካከል መቀሌ  አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም