በባሌ ሮቤ ከተማ አንድ ትምህርት ቤት በአርቲስት ኡመር ሱሌማን ስም ተሰየመ

64

ጎባ ጥር 13/2011 በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ  የሚገኘው  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከዛሬ ጀምሮ በአርቲስት ኡመር ሱሌይማን ስም እንዲጠራ ተሰየመ፡፡

ትምህርት ቤቱ በአርቲስቱ ስም የተሰየመው ባለፉት 20 ዓመታት ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ላበረከተው አስተዋጽኦ ነው፡፡ 

አርቲስቱ የኦሮሞ ህዝብ ትግልን በሙያው በማነቃቃትና የህዝብ አንድነት እንዲጠናከር ላበረከተው አስተዋጽኦ ዛሬ በባሌ ሮቤ መዳ ወላቡ ስቴዲዮም ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ደማቅ  አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

አርቲስት ኡመር ሱሌይማን በዚሁ ወቅት እንደተናገረው በብዙ ዜጎች መስዋእትነት የተገኘውን ለውጥ ለመገደፍ እና ለማጠናከር ወደ ሀገሩ ተመልሷል ።

" ከሀገር ቤት የወጣነው አገራችንን ጠልተን ሳይሆን ጭቆና በዝቶብን ነው ፤ እኔንም ጨምሮ ሁላችንም በያለንበት  በጀግንነት በመታገል አሁን ከቤተሰቦቻችን ጋር እንድንቀላቀል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል " ሲል ተናግሯል።

የአሁኑ ትውልድ ድህነትን ለመዋጋትና ለውጡን ለማስቀጠል በመስዋዕትነት የተገኘውን አንድነት የማጠናከር ታሪካዊ ኃላፊነት እንደተጣለበትም ገልጿል፡፡ 

የኦሮሞ ህዝብ አሁን ያለውን ለውጥ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ጠብቆ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ እንዳለበትም አሳስቧል።  

ህዝቡን በመወከል ንግግር ያደረጉት የሀገር ሽማግሌ ሐጂ አሎ አደም  አርቲስቱን "  እንኳን ደህና ወደ ትውልድ ቀዬህ መጣህ፤  ወጣቱ ትውልድ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በከፍተኛ መስዋእትነት የተገኘውን አንድነትና ሀገራዊ ለውጡን መደገፍ አለበት "ብለዋል፡፡

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀጂ በበኩላቸው  አርቲስት ኡመር የኦሮሞን ሙዚቃ እንዲጎለብት ከማድረግ ባሸገር ህዝቡን ለእኩልነትና ለፍትህ እንዲታገል በማነሳሳት ለውጥ እንዲመጣ የታገለና ያታገለ ጀግና የህዝብ ልጅ  መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ  ፊቱን ወደ ልማት በማዞር በድህነት ላይ በግንባር ቀደምትነት እንዲዘምትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

የባሌ ህዝብም አርቲስቱ ላበረከተው አስተዋጽኦ በስሙ ትምህርት ቤት ከመሰየም ባሻገር የተለያዩ ባህላዊ ስጦታዎችን አበርክቶለታል፡፡ 

ከአስራ ስምንት ዓመታት የውጭ  ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ የተመለሰው አርቲስት ኡመር ሱሌይማን ጭቆናን የሚያወግዙ  ዘፈኖች በማቀንቀን በህዝቡ ዘንድ በስፋት ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም