ከሱልልታ እስከ ጎሀጽዮን ባለው አውራ መንገድ ዳር የሚገኙ የትራፊክ ምልክቶች ለጉዳት እየተዳረጉ ነው

212

ፍቼ ጥር 13/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሱልልታ እስከ ጎሀጽዮን ባለው አውራ መንገድ ዳር የሚገኙ የትራፊክ ምልክቶች ጉዳትና ጥፋት እየደረሰባቸው መሆኑን ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ተናገሩ፡፡ 

ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በአሽከርካሪዎችና በህገወጥ ግለሰቦች ጉዳት እየደረሰባቸው ያለው የማስጠንቀቂያና መረጃ መስጫ ምልክቶች ለረዥም ዓመት አገልግሎት እንዲሰጡ ታልመው የተተከሉ ናቸው፡፡

ቅሬታውን ካቀረቡ ነዋሪዎች መካከል በዞኑ ውጫሌ ወረዳ የሚገኙት አቶ ጀንበር ወሰኑ የትራፊክ ምልክቶች በአሽከርካሪዎች ጥንቃቄ  ጉድለት ተደጋግሞ ጉዳት ሲደርስባቸው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ጉዳት አድራሾችን በህግ ለማስቀጣትም ሆነ ምልክቶቹን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገው ጥረት አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው የተጎዱት ምልክቶች ፈጥነው አለመተካታቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው በቀን ከአራት ጊዜ በላይ እንደሚመላለሱ የገለጹት የሚኒባስ አሽከርካሪው አቶ ግርማ ደሳለኝ በበኩላቸው " በመንገዱና በትራፊክ ምልክቶቹ ላይ በአሽከርካሪዎች ጉዳት ሲደርስ ተከታትሎ የሚያሰራ ተቆጣጣሪ የለም " ብለዋል፡፡

በእዚህም በርካታ የትራፊክ ምልክቶችና ማመላከቻዎች ወድቀው በመጎዳታቸው ለሌላ የትራፊክ አደጋ መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።

ከአዲስ አበባ መውጫ በር ላይ ከፍተኛ ገደል መኖሩን የሚገልጹ አንፀባራቂ ምልክቶች በተሽከርካሪዎች ተገጭተው መውደቃቸውን የተናገሩት ደግሞ የሱሉልታ ወረዳ ትራፊክ ፖሊስ ኢንስፔክተር ከበደ ድንቁ ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ድልድዮች፣ የመታጠፊያ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የከተማ መግቢያዎችና ከፍተኛ ቁልቁለት ያለባቸው ስፍራዎችን ለማመላከት የተተከሉት የትራፊክ ምልክቶች በህገወጦች ተነቅለው መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የመንገዱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ በመንገዱም ሆነ በምልክቶቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ከእዚህ ጎን ለጎን አጥፊዎቹን ለህግ ለማቅረብ በባለስልጣኑ በኩል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከብድርና ከእርዳታ በሚገኝ ገንዘብ የሚሰሩት መንግዶችና የትራፊክ ምልክቶች ያለጊዜያቸው መበላሸታቸው በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርም አመልክተዋል፡፡

ህብረተሰቡ በመንገድ እጦት የሚደርስበትን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተገንዝቦ መንገዶችና የትራፊክ ምልክቶችን በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል፡፡

የትራፊክ ምልክቶቹ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው መሰራታቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ በምልክቶቹ ላይ ጉዳት ሲደርስ በዝምታ ከማለፍ ይልቅ አቅራቢያው ላለው ፖሊስ ማሳወቅ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የዞኑ መንገድ ትራንስፖርት ምክትል ኃላፊ አቶ አመንቴ ረጋሣ በበኩላቸው በመንገድ ዳር ምልክቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳትና መጥፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ችግሩን ለመፍታት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን ጠቁመው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ከአዲስ አበባ መውጫ እስከ ጎሀፅዮን ያለው መንገድ 182 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በጃፓንና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር በአራት ቢሊዮን ብር የተሰራ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም