የቆዳው ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ የማምጣት እና የስራ እድል የመፍጠር ሚናውን እየተወጣ እንዳልሆነ ተጠቆመ

222

አዲስ አበባ  ጥር 13/2011 የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ የማምጣት እና የስራ እድል የመፍጠር ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመለከተ።

የኢትዮጵያ ቆዳ ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶችና ሰራተኞቻቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።

በምክር ቤቱ የንግድና የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቆዳው ዘርፍ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ የኢትዮጵያ ቆዳ ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ጠንካራ ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ቆዳ ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩትን የ2011 ዓ.ም. ሩብ አመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል።

በግምገማው በዘርፉ ያሉ በርካታ ጉዳዮችን የተመለከተ ሲሆን ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማምጣትና የአገር ውስጥ የስራ እድልን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ቢሆንም አፈፃፀሙ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ፈትሿል።

ዘርፉ ላለፉት 6 ወራት የስራ እድል ለመፍጠር ከያዘው ዕቅድ የፈጸመው 42 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ ሲሆን የውጭ ምንዛሬን ከማምጣት ረገድም  አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆኑንም ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደስራ ያለመግባታቸውን የገመገመው ቋሚ ኮሚቴው ወደ ስራ የገቡትም ለወጪ ንግድ ቅድሚያ ሰጥተው እንደማይሰሩ ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ጥራቱን የጠበቀ የቆዳ ግብአት እጥረት፣ ቆዳውን ለማቆየት የሚጠቀሙበት የጨው አቅርቦት በወቅቱና በተገቢው ዋጋ አለመገኘቱ ለዘርፉ መቀዛቀዝ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን አመላክቷል።

የቆዳ ፋብሪካዎች ከአየር ንብረት ብክለት ጋር ተያይዞ ጥያቄ የሚነሳባቸው መሆኑና በቅርቡም አራት ፋብሪካዎች ምርት እንዲያቆሙ መደረጉም እንደ ችግር የተነሳ ሲሆን በቀጣይም አካባቢን እየበከሉ የሚያመርቱበት ምንም አይነት አሰራር አይኖርም ሲል ቋሚ ኮሚቴው አጠቃሏል።

በዘርፉ ከላይ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ኢንስቲትዩቱ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦጋለ ፈለቀ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶችና ሰራተኞቻቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግ አኳያም እስካሁን በተደረገው ክትትልና ድጋፍ ከ12 የአገር ውስጥ የቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ ስምንቱ የሁለተኛ ደረጃ የተረፈ ምርት ማጣሪያ እንዲገነቡ ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሞጆ አካባቢ የሚገነባው የኢትዮጵያ መንግስት የሞጆ የጋራ ፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት በፍጥነት እንዲገነባ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከተነደፈ የቆየ ቢሆንም በፕሮጀክቱ ላይ የጠራ አመለካከት ባለመኖሩ ምክንያትና የመሬት፣ የዲዛይንና የካሳ ጉዳዮች እንዳጓተቱት ታውቋል።

በተለይ በቅርቡ በሞጆ የቆዳ ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ ከተወሰደ ወዲህ ፕሮጀክቱ እንዲገነባ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ መጀመሩንና በፕሮጀክቱ ላይ የጠራ ግንዛቤ ኖሮ የዲዛይን የማሻሻል ሂደቱ እየተገመገመ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱን ለመገንባት 85 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠይቅ ሲሆን ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለፕሮጀክቱ ግንባታ 15 ሚሊዮን ዩሩ በድጋፍ እና 35 ሚሊዮን ዩሮ በብድር ባጠቃላይ 50 ሚሊዮን ዩሮ እስካሁን መገኘቱንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

የቀረው ወጭ በመንግስትና በሌሎች የልማት አጋሮች እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

ይህ ተግባር ሲጠናቀቅ ፋብሪካዎቹ ከአካባቢ ብክለት ጋር የሚነሳው ጥያቄ የሚመለስ ይሆናል ያሉት ዳይሬክተሩ በራሳቸውም ያለባቸውን ችግር ለመፍታት መጣር ይኖርባቸዋል ብለዋል።