'መንግስት የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል' _ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ

87
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2010 የኢትዮጵያ መንግስት የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ። አገራዊ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገቱን አጠናክሮ ማስቀጠል ይቻል ዘንድ ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዘብ እንዲቆምም ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቱ ጥሪውን ያቀረቡት ነገ የሚከበረውን 27ኛ ዓመት የግንቦት ሃያ የድል በዓል አስመልክቶ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ በዚሁ መልዕክታቸው "የግንቦት ሃያ ድልን ማስቀጠል፣ ማስጠበቅና የዴሞክራሲ ሜዳውንም የበለጠ በማስፋት የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች የመመለስ ተግባር ዋነኛው የመንግስት ትኩረት ነው" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት መንግስት እያገኘ ያለው የሕዝብ ድጋፍ የግንቦት ሃያ ድሎችን ለማስፋት አንድ ተጨማሪ ኃይል እንደሚሆነውም  ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። የበለጠ አገራዊ ልማትና ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ ሰላም ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ አክለውም በኢትዮጵያ የተመሰረተው ፌደራላዊ ስርዓት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ ለዘመናት የአገሪቱ ዋነኛ መለያ ሆኖ የቆየውን ድህነት ለመዋጋት ባለፉት ዓመታት የተደረገው ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ አስችሏል ብለዋል። ከድህነት ጋር የተያያዙ ችግሮች አሁንም ድረስ የሚስተዋሉ ቢሆንም፤ የጉስቁልናና የረሃብ ምሳሌ የነበረችው ኢትዮጵያ ግን በሚያስገርም ሁኔታ በዓለም ፈጣን የምጣኔ ኃብት እድገት ካስመዘገቡ ጥቂት አገሮች መካከል ለመጠቀስ መቻሏን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ለአገራዊ ህልውና ጭምር አደጋ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ የሆነ  ሰላምና መረጋጋት እውን ማድረግ መቻሉን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። ባለፈው የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስጋቱ በከፍተኛ መጠን በጨመረበት ወቅት በብዙ የአፍሪካ አገሮች ባልተለመደ መልኩ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማድረግ  ኢትዮጵያ ለአህጉሩ ተምሳሌትነቷን ማሳየቷንም ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም