አፄ ሚኒሊክንና የድል ስራዊታቸው የሚያስታውስ ሀውልት በወረኢሉ ሊገነባ ነው

94

ደሴ ጥር 12/2011 የአደዋ በጎ አድራጎት ማህበር አፄ ሚኒሊክንና የድል ስራዊታቸውን የሚያስታውስ ሀውልት በወረኢሉ ከተማ ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡት ስድስተኛው የአድዋ የእግር ጉዞ የሚያደርጉት የልኡካን ቡድን አባላት ትናንት ወረኢሉ  ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ያሬድ እሸቴ በዚህ ወቅት " የጥንት አባቶቻችን ታሪክ ለማስታወስ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ለማስቀጠል፣ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶቻችን ለማዳበር ማህበሩ ተመስርታል ብሏል።

የካቲት 23 የአደዋን ድል በዓል በእግር ተጉዘው ለማክበር 14 የማህበሩ አባላት ጥር 1/2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ተነስተው ወረኢሉ ከተማ ገብተዋል፡፡

ወጣቱ እንዳለው ለአደዋ ድል መነሻና  የክተት ጥሪ አዋጅ መሰረት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ባህር ተሸግሮ የመጣውን ጠላት ለመመከት በመከሩባት ወረኢሉ ከተማ የአፄ ሚኒሊክና ሰራዊታቸው የሚያስታውስ ሀውልት በህብረተሰቡ ትብብር ለመገንባት የመሰረተ ድንጋዩ ተቀምጧል።

እስካሁን በተደረጉ የእግር ጉዞዎች የድል መነሻዋን ታሪካዊ ከተማ ሳይጎበኙ በመቅረታቸው መቆጨታቸውን አስታውሶ፤ ህብረተሰቡ በተለይው ወጣቱ የጥንት አኩሪ አባቶችን ታሪክ በመድገም ለሀገር አንድነት እጅ ለእጅ ተያይዞ ለሰላም እንዲተጋም መልዕክቱን አስተላልፋል።

በደረሱበት ከተሞች  ሁሉ ህብረተሰቡ ላደረገላቸው  መልካም አቀባበልና ድጋፍም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የወረኢሉ ከተማ ከንቲባ አቶ እሸቴ ታረቀኝ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር በመተባበር ሀውልቱን ለማሰራት በርትተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

ስድስተኛው ጉዞ አደዋ ተሳታፊዎች በከተማቸው በማለፋቸውን ህብረተሰቡ በደስታ መቀበሉንና  ወደፊትም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ታሪክ እንዳይጠፋ  አፄ ሚኒሊክንና ስራዊታቸውን  ለማስታወስ አድዋ ላይ የሚሰራው የፓን አፍሪካኒዚም ዩንቨርሲቲ ቅርንጫፉን ወረኢሉ ሊከፍት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ከከተማው የተወጣጡ ዘጠኝ  ወጣቶችም  በእግር ጉዞ መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ እስሌማን እሸቴ  ከክልልና ፌደራል መንግስት ጋር በመምከር  ሀውልቱን ለማሰራት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡

" ታሪካችን በማስታወስ ኢትያጵያዊ አንድነታችን ለማጠናከር ወጣቶች የሚያደርጉት በጎ ተግባር ሊበረታታ ይገባልም " ብለዋል፡፡

የአድዋ የእግር ጉዞ የሚያደርገው የልኡካን ቡድን አባላት ህብረተሰቡ በደማቅ ሁኔታ እንደተቀበላቸው  ሁሉ ዛሬ በደማቅ አሸኛኘት የተሳናበታቸው  ሲሆን ጥር 14/2011ዓ.ም. ደሴ ከተማ ሲገቡ ተመሳሳይ አቀባበል ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

ስድስተኛው ጉዞ አደዋ ማህበር አባላት የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን በቀን እስከ 50 ኪሎ ሜትር በመጓዝ የካቲት 23 የአድዋን የድል በዓል በቦታው በመድረስ እንደሚያከብሩ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም