በአሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ከሻይ ቅጠል ምርት 1 ሚሊዮን ብር ገቢ አገኙ

125

መቱ  ጥር 12/2011  በኢሉአባቦር ዞን አሌ ወረዳ በሻይ ልማት የተሰማሩ አርሶአደሮች ባለፉት ስድስት ወራት  ለገበያ ካቀረቡት የሻይ ቅጠል ምርት ሽያጭ 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ፡፡

የዞኑ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን እንደገለጸው ምርቱን ለገበያ ያቀረቡት በወረዳው በግልና በማህበር ተደራጅተው በልማቱ የተሰማሩ 234 አርሶአደሮች ናቸው፡፡

ለገበያው ያቀረቡት  የሻይ ቅጠል ምርት  መጠን 216 ሺህ 600 ኪሎ ግራም መሆኑን በባለስልጣኑ የቡናና ሻይ ልማት ቡድን መሪ ተወካይ  አቶ ተስፋዬ ሶኔሳ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሮቹ  ምርቱን ለገበያ እያቀረቡ ያሉት በአካባቢው ከሚገኝ የጉመሮ ሻይ ልማት ድርጅት ጋር በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር አማካኝነት ነው ።

በስድስት ወራት ውስጥ ካቀረቡት የሻይ ቅጠል ምርት ሽያጭ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ አግኝተዋል፡፡

በወረዳው  በሻይ የሚለማውን 259 ሄክታር  መሬት በመጪው ክረምት ወደ 270 ሄክታር ለማሳደግ ታቅዶ  እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

የሙያ እገዛና ድጋፍ በመስጠትም የልማቱ ተሳታፊ አርሶአደሮችን ቁጥር ወደ 900 ለማሳደግም ታቅዳል፡፡

አርሶ አደር እንዳለ ብርሀኑ በወረዳው የጉመሮ ቀበሌ  ነዋሪ ሲሆኑ  ከመደበኛው የግብርና ልማት ስራቸው  በተጓዳኝ የሚያለሙት ሻይ ገቢያቸውን በማሳደግ ለተሻለ ኑሮ እንዲበቁ እንዳገዛቸው በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

በዓመቱ  ለጉመሮ ሻይ ልማት 2ሺ 500 ኪሎግራም  የሻይ ምርት አቅርበው ከ10 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ከሚያለሙት ሻይ ቅጠል  በየዓመቱ እስከ 30 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ እየሆኑ የተናገሩት ደግሞ የኦንጋ ቀበሌ አርሶአደር አለም ገላ ናቸው፡፡  

በቡና እና ሻይ ልማት  የሚገኘው ገቢ ከሰብል ልማቱ እንደሚበልጥ ገልጸው አርሶ አደሩ  ልማቱን በማስፋፋት ለተሻለ ጥቅም እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

አሌ በኦሮሚያ ክልል  የሻይ ቅጠል ልማት በአርሶአደር ደረጃ የሚካሄድባት ብቸኛ ወረዳ ናት ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም