“አባቴን የሚቀይረው ልብስ ሳያስቀሩ ዘርፎውታል”

53

ጥር 11/2011 አቶ ታደሰ አባተ ይባላሉ። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የሚኖሩት የ88 ዓመት አዛውንት አቶ ታደሰ አንድ ቀን ያላሰቡት ነገር ይገጥማቸዋል።

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ እንደሆነ ይናገራሉ። የእሳቸው ቤት ተዘርፎ ያገኛሉ። አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ የኤሌክትሮንክስ እቃዎችና አምስት መቶ ብር ይወሰድባቸዋል። እንዴትና ማን እንደዘረፋቸው ግን እስካሁን አላወቁም።

የአቶ ታደሰ ልጅ እና ጧሪያቸው የሆኑት ወ/ሮ የውብነሽ ታደሰ “አባቴን የሚቀይረው ልብስ ሳያስቀሩ ዘርፎውታል” ይላሉ። 

ወይዘሮ ውብነሽ እንደሚሉት በአከባቢው ማንነታቸው የማይታወቁ በርካታ ተከራዮች አሉ። በአከባቢው ለሚከሰት ተደጋጋሚ ዝርፍያ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ነው ጥርጣሬያቸውን የገለጹት።

የአባቴ ዘራፊዎች ከሩቅ የመጡ ሊሆኑ አይችሉም የምሉት ወይዜሮ የውብነሽ፤ ቤት የሚያከራዩ ሰዎች ከዚህም የከፋ ወንጀል እንዳይፈፀም የተከራዮችን ማንነት ማወቅ እንደሚጠበቅባቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሌላዋ በተመሳሳይ በዚሁ አካባቢ የምኖሩ የችግሩ ሰለባ የሆኑት የአንድ ልጅ እናት ወ/ሮ ፍሬህይወት ሽመልስ  ናቸው።

ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ወይዘሮ ፍሬህይወት የሚኖሩበት ቤት በር ከፍተው ይገባሉ። በሽጉጥ አስፈራርተው ሁለት ሞባይሎችን፣ ስድስት መቶ ብር የያዘ ቦርሳና የተለያዩ እቃዎችን አይናቸው እያየ እንደተወሰደባቸው ይናገራሉ።

"በወቅቱ ብጮህም የሚደርስልኝ ጎረቤት አጣሁ" የምሉት ወይዜሮ ፍሬህይወት “የ9 ዓመት ልጄ እንዳይጎዳብኝ በመፍራት እያየሁት ተዘርፌያለሁ’’ ነው ያሉት።

ለማስፈራሪያነት የተጠቀሙበት ሽጉጥ ግን የውሸት እንደሆነ አረጋገጡ።   ዘራፊዎቹ ጉዳያቸውን ከጨረሱ በኋላ ለማስፈራሪያነት የተጠቀሙትን ሽጉጥ የሚመስል መሳሪያ በቤታቸው ደጃፍ ላይ ጥለውት ሄደዋል።

ወይዘሮ ፍሬህይወት ዘራፊዎቹ ለማስፈራሪያነት የተጠቀሙት ሽጉጥ የሚመስል መሳሪያ የውሸት መሆኑን ያወቁት ንብረታቸው ላይመለስ ሰዎቹ ከተሰወሩ በኋላ እንደሆነ ያስታውሳሉ። ”ጅብ ከሄ ውሻ ጮሄ” እንደሚሉት ማለት ነው።

አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ወይዜሮ ፍሬህይወት የቤታቸው በር የውስጥ መዝግያ የለውም፤ በራቸውን የተለያዩ እቃዎች በማስደገፍ ይዘጋሉ። ዘረፋ የተፈፀመበት ቀንም በተመሳሳይ ሁኔታ ነበር የዘጉት።

“ከተወሰደብኝ ንብረት በተጨማሪ እኔና ልጄ የደህንነት ስጋት ውስጥ ገብተናል” ያሉት ወይዜሮ ፍሬህይወት የሚመለከተው አካል ለእነዚህ  ስጋቶች ቶሎ  መፍትሔ ልሰጥ ይገባል ይላሉ።

ወይዜሮ ፍሬህይወት ጉዳዩን ለፖሊስ በወቅቱ ብያመለክቱም ምርመራ ከማካሄድ ያለፈ እስካሁን ምንም ውጤት እንዳልተገኘ  ይገልጻሉ።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ደስአለ አድማሴ እንደሚሉት በአከባቢው የሚገኙ የጽጥታ አከላት የፓትሮል ስራ የሚሰሩት እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ቢሆንም በአብዛኛው ወንጀል የሚፈፀመው  ሌሊት ከስድስት ሰዓት በኋላ ነው።

ህብረተሰቡ ወንጀል ለመከለካል ከፀጥታው አካላት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ልምድ አናሳ ነው ያሉት አቶ ደስአለ ወንጀልን የመከላከል ስራ በዋናነት የህብረተሰቡ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋሉ ዝርፍያዎችን ለመከላከል ህብርተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ የአዲስ አባባ ፖሊስ ኮሚሽን ይገልጻል።

በኮሚሽኑ ኢንዶክትሬሽን እና  ህዝብ ግንኙነት ም/ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ  እንዳሉት ለህዝብ ስጋት የሚሆኑ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስውር እና ግልፅ ጥበቃዎች ተሰማርተዋል።

እነዚህን ጥበቃዎች በማሰማራት እንዲሁም ጥናት እና ክትትል በማድረግ በርካታ ወንጀል ፈጻሚዎችን በመያዝ ወደ ፍርድቤት እየቀረቡ እንደሆነም ኮማንደር ፋሲካ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ በጦር መሳሪያ ዘረፋ፣ በቀን እና ሌሊት በውንብድና ድርጊት እና በመኪና ስርቆት የተሰማሩ በማእከል ወንጀል ምርመራ ጥናት ተደርጎ እጅ ከፈንጅ የተያዙ 21 ተከሳሾች ላይ ክስ  መመስረቱንም ኮማንደሩ ገልጸዋል።

በከተማዋ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት የሚስተዋል መሆኑን የተናገሩት ኮማንደር ፋሲካ  በጦር መሳሪያ የታገዘ ዝርፍያ እየሰፋ መቷል ይላሉ።

ህብረተሰቡ በአከባቢው የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከፀጥታ አስከባሪ ሃይሎች ጋር በመሆን ወንጀለጆችን የማጋለጥ ስራ ሊያከናው እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም