ፖሊስ በከተራና ጥምቀት በዓል አከባበር ህብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር አመሰገነ

76

አዲስ አበባ ጥር 11/2011የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተራና ጥምቀት በዓል አከባበር ህብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር ምስጋናውን አቀረበ።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በጥምቀት በዓል አከባበር በርካታ ቁጥር ያላቸው የኃይማኖቱ ተከታዮች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉ የውጪ ሀገራት ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ሀገራት ቱሪስቶች ታድመውበታል።

በመሆኑም በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ስፍራዎች በተለይም በጃን ሜዳ የተከበሩት የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም ተከብሯል።

በተያዘው ዓመት በርካታ ህዝብ የታደመባቸው ሃይማኖታዊ እና ስፖርታዊ ዝግጅቶች በሰላም መከበራቸውን ያስታወሰው የኮሚሽኑ መግለጫ የከተራና የጥምቀት በዓላትም ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል ብሏል።

ለዚህም ህብረተሰቡ በዋናነት ደግሞ የአዲስ አበባ ወጣቶች ለሰላሙ  መረጋገጥ  እያበረከቱት ላለው ቀና ትብብር ኮሚሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል።

በነገው እለት ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዩች የሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓልም በሰላም እንዲከበር ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም