በሙምባይ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል

87

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 በህንድ ሙምባይ ነገ በሚካሄደው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል።

ውድድሩ ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ነው።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሰለሞን ደቂሳና አማን ጎበና በባለፈው ዓመት የሙምባይ ማራቶን በቅደም ተከተል በወንዶችና በሴቶች ውድድር ማሸነፋቸው ይታወሳል።

በዘንድሮው ውድድር በወንዶች አትሌት አበራ ኩማ እና በሴቶች አትሌት አማን ጎበና የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት እንዳገኙ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።

አትሌት አበራ ባለፈው ዓመት በኔዘርላንድ በተካሄደው የሮተርዳም ማራቶን 2 ሰአት ከ5 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ ያሸነፈበት ጊዜ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱ ሲሆን በነገውም ውድድር ከሚሳተፉ አትሌቶች የተሻለ የግል ምርጥ ሰአት አለው።

"በጣም ጥሩ የሚባል ልምምድ ሳደርግ ቆይቻለሁ በነገው ውድድር ከግል ምርጥ ሰአቴ የተሻለ ጊዜ ለማስመዝገብ እሮጣለሁ" ሲል ከውድድሩ በፊት በሰጠው አስተያያት ገልጿል።

በ2018 ዓ.ም በአቡዳቢ ማራቶንና በበርሊን ማራቶን አቋርጦ የወጣበትን ጊዜ ረስቶ ለነገው ውውድር በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝና ይህንንም ውድድር ለማሸነፍ እንደተዘጋጀ ተናግሯል።

አትሌቱ የቦታውን ክብረ ወሰን የማሻሻልም እቅድ እንዳለው ተናግሯል።

የአበራ ኩማ ታናሽ እህት አትሌት ዲባባ ኩማ በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም በህንድ ካልካታ ከተማ በተካሄደ የ25 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ማሸነፏን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በዘገባው አስታውሷል።

በሴቶች የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ አትሌት አማን ጎበና እ.አ.አ በ2016 በቶኪዮ ማራቶን 2 ሰአት ከ21 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ ሁለተኛ የወጣችበት ጊዜ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷ ነበር።

"የባለፈው ውድድር በጣም ያስደሰተኝና የረካሁበት ነው የነገውንም ውድድር በጉጉት እጠብቃለሁ አሁን እድሜዬ 36 ነው ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ እየሮጥኩ ነው" ብላለች።

በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች እያንዳንዳቸው የ45 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን የቦታውን ክብረ ወሰን ከሰበሩ ተጨማሪ የ15 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኛሉ።

በሌላ በኩል ነገ በስፔን ሲሺያ በሚካሄደው "የክሮስ ኢንተርናሲዮናል ዲ ኢታሊሳ" የአገር አቋራጭ ወድድር በሴቶች የ6 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጌጤ አለማየሁ ትሳተፋለች።

በወንዶች የ11 ኪሎ ሜትርና በሴቶች የ6 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ውድድር የዩጋንዳና የኬንያ አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል።

"የክሮስ ኢንተርናሲዮናል ዲ ኢታሊሳ" የአገር አቋራጭ ወድድር በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፈቃድና እውቅና የተሰጠው ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም