"የጥምቀት በዓል ልዩ ትእይንት ነው" -የበዓሉ ታዳሚ የውጭ ዜጎች

112

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው ዓመታዊ የጥምቀት በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ በጃን ሜዳ በታላቅ ስነ-ስርአት ተከብሯል።   

በዓሉ በተለያዩ የባህል አልባሳት የተዋቡ ታዳሚዎች፣ ዘማሪያንና ቀሳውት ታጅቦ የፈረስ ጉግስና ባህላዊ ጭፈራም ደምቆ መከበሩ በተለይ የውጭ አገር ቱሪስቶችን ቀልብ ስቧል። 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ አገር ቱሪስቶች እንደሚሉት ኃይማኖታዊ መዝሙሩ፣ባህላዊ ጭፈራውና ትዕይንቱ በእጅጉ ቀልባቸውን ገዝቶታል።

ጎብኝዎቹ በኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ አቀባበል እንደተማረኩ እንዲሁም ቤታቸው ያሉ ያህል ተሰምቷቸው በዓሉን በልዩ ስሜት ማክበራቸውን ተናግረዋል።      

የጥምቀት በዓል ሁሉም ጎብኝ ሊታደምበት የሚገባ በዓል መሆኑንም ነው የሚገልጹት ጎብኝዎቹ።   

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓሉን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የጀመረው ጥረት የሚበረታታና በበርካታ ቱሪስቶች እንዲጎበኝ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ይናገራሉ። 

ከእስራኤል የበዓሉ ታዳሚ የሆኑት ዴቪድ ሱዳይ በኣሉ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው ይመስለኛል ምክንያቱም በዓሉ ልክ አፍሪካን እንደ አምባሳደር የሚወክል ነው በቀጠናው ለሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮችም አምባሳደር ነው ይሄ በዓሉ የሚከበርበት ቦታ በዩኔስኮ መመዝገቡ በጣም ጠቃሚ ነው በዓሉ እንዲመዘገብ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡

"አይሁዳዊ ነኝ ክርስቲያን አይደለሁም፤ያም ቢሆን ዝማሬው ኃይማኖታዊ ስርአቱ የሰዎቹ አለባበስ በዓሉ እራሱ ያለው ኃይል ይስባል፤ ያለው ኃይል የእምነቱ ተከታይ ባትሆንም የበዓሉ አካል እንድትሆን ያደርጋል" ነው ያሉት እስራኤላዊው የበዓሉ ታዳሚ።  

በዚህ በዓል ላይ በመገኘታቸው እድለኝነት እንደሚሰማቸውና በዓሉ የሚከበርበት መንገድ አስገራሚና የተለየ እንደሆነም ገልጸዋል። 

ከጀርመን ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ክርስቶፍ ሩፕ በበኩላቸው    በአገሬ የተለያዩ ቦታዎች በዩኔስኮ ቅርስነት ተመዝግበዋል ጥምቀትም ቢመዘገብ ከዓለም ይበልጥ እውቅና ያገኛል ዓለም አቀፋዊ ይሆናል ዓለም አቀፋዊ ይዘት ይኖረዋል ብዙ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ የጥምቀት አከባበር የሚያውቁ አይመስለኝም በተጨማሪም ብዙ ቱሪስቶችን መሳብ ይችላል ይህም ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል ብለዋል፡፡

ሌሎች በጀርመን የሚኖሩ ጉዋደኞቼ በበዓሉ ላይ እንዲሳተፉ መጋበዝ እፈልጋለሁ ሲልም ሀሳቡን አጋርቷል።

የከተራና የዛሬው የጥምቀት በዓል አስደሳችና ማራኪ የሆነ የኃይማኖታዊ ስርአት እንደሆነ መገንዘቡንም ነው ክርስቶፍ የሚገልጸው።

ከስዊድን የበዓሉ ታዳሚ ክላሴ ሳህሌን ለኢትዮጵያ በዓሉ መመዝገቡ እንዴት ይጠቅማታል በሚለው ነገር ሙያዊ አስተያያት መስጠት አልችልም፤ ነገር ግን  የመመዝገቡ ነገር እውን ቢሆን ትልቅ ኩራት ነው የሚሰማኝ የዚህ በዓል አካል መሆኔም ያስደስተኛል።

የጥምቀት በዓል በጣም ታላቅ የሚባል ኃይማኖታዊ የአከባበር ስርአት እንደሆነና እንደዚህ አይነት የበዓል አከባበር በስዊድን እንደሌለም ተናግረዋል። 

የእንግሊዝና የስዊዘርላንድ ጥምር ዜግነት ያላት ዶሪስ ጆንሰን በበኩላ ላለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ እንደኖረች ተናግራ  በአገሪቷ ከሚከበሩ የኃይማኖት በዓላት የጥምቅት በዓል ትኩረቷን የሳበውና አስደናቂ እንደሆነ ገልጻለች። 

ከዚህ በተጨማሪም በዓሉ እጅግ በጣም ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው የነገሩን ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችም አሉ።  

በጃን ሜዳው የጥምቀት በዓል ላይ በ100ዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገር ዜጎች የታደሙ ሲሆን በአጠቃላይ በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከ15 ሺ በላይ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የጥምቀቱ በዓል በድምቀት የተከበረ ሲሆን፤ ከተለያዩ ገዳማትና አድባራት የወጡት ታቦታትም በምዕመናኑ ታጅበው ወደ መንበራቸው ተመልሰዋል። 

በትናንትናውም ዕለት የከተራ በዓል በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ -ስርዓት መከበሩ ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም