የጥምቀት በዓል በማይጨው ከተማ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከበረ

83

ማይጨው ጥር 11/2011 የጥምቀት በዓል በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በማይጨው ከተማ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከበረ።

በከተማው ከ40 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ጨምሮ ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ከመሃል አገርና ከውጭ ሀገር የመጡ እንግዶች በበዓሉ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዴስቆርዮስ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኗ ለረጅም ዘመናት የምታከብረው የጥምቀት በዓል ሳይበረዝና ሳይከለስ ወደ ትውልድ ማሸጋገር ይገባል፡፡

"ሰላም ከሌለ የጥምቀት በዓልን እንዲህ ተሰባስበን ማክብር አንችልም" ያሉት አቡነ ዴስቆርዮስ፣ የእምነቱ ተከታዮች ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ግጭት ልማትን ሳይሆን፤ ጥፋትን እድገትን ሳይሆን ውድመትን እንደሚፈጥር የተናገሩት አቡነ ዴስቆርዮስ፣ የሕዝቡ ፍላጎት ሰላም በመሆኑ የፖለቲካ መሪዎች ልዩነታቸውን በማጥበብ ለሰላምና እድገት መነሳት አለባቸው ብለዋል፡፡

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በበኩላቸው መንግሥት የአካባቢውን ሕዝብ ሰላም በማስጠበቅ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል፡፡

የከተማው ነዋሪዎች በተለይ ወጣቶች የአካባቢውን ፀጥታ በመጠበቅ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ከዋዜማው ጀምሮ የራያ ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ ሆራና ባህላዊ ጭፈራዎችን በመጫወት ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተዋል፡፡

ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች መንፈሳዊ ዝማሬዎችን አሰምተዋል፡፡

ታቦታቱ ባደሩበት የማይጨው ቅዱስ ተክለሃይማኖት ገዳም ምዕመኑን የማጥመቅ ሥነ ሥርዓት ተካሄዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም