አዲሱ ትውልድ የኢትዮጵያዊነት ባህልን ጠብቆ የማስተላለፍ ሃላፊነትን ሊወጣ ይገባል - የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

95

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 አዲሱ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከበውን የኢትዮጵያዊነት ባህል ለትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ።

ሚኒስትሯ የጥምቀት በዓልን አስመልክተው በጃንሜዳ ባደረጉት ንግግር "አባቶቻችን ከተለያዩ ክብረ በዓላት ጋር አብረው ያስረከቡን የአለባበስ፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የይቅር ባይነት ባህል" አሁንም በርካታ ቱሪስቶችን ወደ ኢትዮጵያ እየሳበ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ይህን ከግምት በማስገባት ለባህል ጥበቃና ልማት ትኩረት ሰጥቶ በተግባር የሚታይ ድጋፍም እያደረገ መሆኑን አሳውቀዋል።

"ኢትዮጵያዊ ባህሎችና ጥበቦች የኢትዮጵያዊያን ብቻም ሳይሆኑ የአለም ሃብት የሚሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰናል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ የጥምቀት በዓልን የአለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በአሉን ብለው የሚመጡ እንግዶችንም በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት "ባህል ልንቀበላቸውና ልናስተናግዳቸው ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያዊነት ባህላችን ሳይበረዙ እንዲቆዩና እንዲጠበቁ ሁሉም የራሱን ድርሻ እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የጥምቀት በዓልን በሰው ልጆች ወካይ የዓለም ቅርስነት የማስመዝገቡ ውጤት በመጪው ዓመት እንደሚታወቅ መግለጹን ኢዜአ ሰሞኑን መዘገቡ ይታወሳል። 

የጥምቀት በዓልን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም