የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲተጉ ጥሪ ቀረበ

127

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም  ለሚያስጠብቁ ጉዳዮች   ትኩረት በመስጠት ፈጥነው ወደተግባር መግባት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

ፕሬዘዳንቷ ማሳሰቢያውን ያስተላለፉት ላለፈው አንድ ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ጋር በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ላይ ሲመክሩ ለቆዩት አምባሳደሮች ትናንት ምሽት በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚሁ ንግግራቸው አምባሳደሮቹ በየጊዜው የሚቀያየረውን የዓለም የፖለቲካ ሁኔታ በመረዳትና በመተንተን ከኢትዮጵያና ከህዝቦቿ ጥቅም ጋር አጣጥመው መሄድ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናና በተለያዩ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ መድረኮች ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቷን ጠቅሰው ይህንን ተግባር ማስቀጠል ዋና ስራ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በአሁኑ ወቅት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዘዳንቷ "አምባሳደሮቹ ይህን በማስተባበር ረገድ ፈጥነው ወደ ተግባር ሊገቡ ይገባል"  ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ በውጭ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ለመርዳት የተነሳሱበት ጊዜ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ጠቅሰዋል።

"አገሩን ለመደገፍ በከፍተኛ ስሜት የተነሳሳውን ይህንን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማስተባበር ይኖርብናል፤" በዚህ ረገድ በተለይም ዲፕሎማቶቹ ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅባቸው ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያስገነዘቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ "ዓለም ዓቀፍ አዝማሚያዎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ" በሚል ርዕስ  በኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚሰሩ ዲፕሎማቶች ገለፃ አድርገዋል።

መንግስት የዲፕሎማሲ ስራውን አሁን ካለው  አገራዊና የዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የውጭ ግንኙነት ፖለሲውን እንደሚያሻሽል   ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት አንስተዋል።

በተለይም በአገር ውስጥ በከፍተኛ የስራ ሃላፊነት የነበሩ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከሃላፊነት ሲነሱ አምባሳደር እየተደረጉ መሾማቸው ለትችት ሲዳርግ ቆይቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው ግን የአምባሳደሮች ሹመት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም