ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

128

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ከሚያሳዩት በዓሎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው "ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!" ብለዋል።

"ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ይህንን በዓል እንድናከብር ሥርዓት ሲሠሩ በአንድ በኩል በትህትና ስለ ዝቅ ማለት እና ስለ መለወጥ፣ በሌላም በኩል ደግሞ ስለ መደመር ሊያስተምሩን የፈለጉ ይመስለኛልም" ብለዋል።

በዓሉ የመለወጥ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለወጡት ውስጥም አንዱ ውኃ እንደሆነና የሰው ልጅ ከውሀው መለወጥ በፊት በነበረው ታሪኩ ውኃን የሚያስታውሰው በቁጣ መሣሪያነቱ እንደሆነም ገልፀዋል።

"እናም የሰው ልጅ በውኃ ጠፍቷል፤ አሁን ግን ክርስቶስ ወደ ውኃው መጣ፤ የመዓቱን ውኃ የምሕረት አደረገው በማለት በሀገራችንም ሕዝባችን በክፉ የሚያስታውሳቸው አያሌ ሞያዎችና ተቋማት አሉ" ብለዋል።

በቢሮክራሲያቸው፣ በግፋቸው፣ በማሰቃያነታቸው፣ በሰብአዊ መብት ጥሰታቸው፣ በአሳዳጅነታቸው፣ በኢፍትሐዊነታቸው፣ በአድሏዊነታቸው፣ ለተወሰኑ አካላት ጥቅም በመቆማቸው የተነሣ በመዓት የምናስታውሳቸው ተቋማት አሉን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ሆኖም አሁን የሚሻለን ምርጫ አልባ ምርጫ እነዚህን የክፋት መታወሻዎች እንደ ውኃው ሁሉ ወደ በረከትነት መቀየር በመሆኑ ለመዓት የነበረው ውኃ ለምሕረት እንደተለወጠው ሁሉ በክፉ ሥራቸው የምናስታውሳቸውን ተቋሞቻችንንም ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ አድርገን እንለውጣቸው ብለዋል፡፡

ተቋማቱን ሕጋቸውን፣ አሠራራቸውን፣ አደረጃጀታቸውን፣ ዕሴቶቻቸውን፣ አስተሳሰባቸውንና አካሄዳቸውን ሁሉ ለፍትህ እና ለእኩልነት ወደ ወገነ መልክ ልንለውጣቸው ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ትኩረታችንን በለውጥ ሥራችን ላይ አድርገን፣ የሚመጡብንን የግራ ቀኝ ጉሸማዎች እያለፍን፣ በሙሉ ዐቅማችን የሚገባንን ከሠራን የምፈልገውን ማግኘታችን አይቀሬ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከቦታችን ሊያናውጡን፣ ከዋናው ተልዕኳችን ሊያዘናጉን ብዙ እንቅፋቶች ሊፈታተኑን ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በብዙ መሰናክሎች ተከቦ፣ ሜዳልያውን እያሰበ፣ ወደ ሩጫው ፍጻሜ እንደሚገሠግሥ ሯጭ ከፊታችን ያለውን ውብ ቀን እና በጥረታችንም የምናስመዘግበውን ጣፋጭ ድል እያሰብን በጽናት ልንሮጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በጊዜያዊ እና አልፎ ሂያጅ ነገሮች ላይ ማተኮር ውጤታችንንም ታሪካችንንም ጊዜያዊ አድርጎት ስለሚቀር በልፋታችን፣ በትግላችን እና በብርታታችን የምንቋደሰው ድል የሁላችንም የመሆኑን ያህል ተግዳሮት እና ፈተናውም የሁሉም ኢትዮጵያ ልጆች እንቅፋት መሆኑን በመረዳት እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅር እና በመደመር ልንሻገረው ይገባል ብለዋል፡፡

በዋናው ተልዕኳችን ላይ አተኩረን ጋሬጣዎችንና ዕንቅፋቶችን ካለፍናቸው ከባሕር ወለል በታች የጀመርነውን ለውጥ ከከፍታ በላይ እንጨርሰዋለንም ነው ያሉት።

የምንጠብቀውም ሆነ የማንጠብቀው ችግር ከምንጓጓለት ግብ እንዳያስቀረን ትኩረታችንን በለውጥ ሂደታችን ላይ ካደረግን በጥምቀት መስክ ላይ የምናያትን ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ላይ እናያታለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም