ኢትዮጵያ ጥምቀትንና ሌሎች ክብረበዓላትን ለዓለም በማስተዋወቅ ጎብኝዎችን መሳብ አለባት­–የውጭ ዜጎች

835

ጥር 10/2011 ኢትዮጵያ ጥምቀትን የመሳሰሉ ክብረበዓላትን ለዓለም በማስተዋወቅ ጎብኝዎችን መሳብ እንዳለባት­-የጥምቀት ከተራ በዓልን ለማክበር የተገኙ የውጭ ዜጎች ተናገሩ፡፡

በጃንሜዳ የጥምቀትና ከተራ በዓልን ለማክበር የተገኘችው ጣሊያንያዊቷ ጆአና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣች በመናገር በዓሉ በጣም ደማቅና የተለየ ሥሜት እንደተሰማት ነው የገለፀችው፡፡

“ኢትዮጵያውያን ደስ ሚሉ ናቸው፤ ወደ ጣሊያን ስመለስም የሀገሬ ሰዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና የጥምቀትን በዓል እንዲያዩ እነግራቸዋለሁ” ብላለች፡፡

የጥምቀት በዓል ጎብኝዎችን ለመሳብ ፋይዳው የላቀ ነው ያለችው ጆአና መንግስትና ህዝቡ በዓሉን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባቸው ተናግራለች፡፡

በዓሉ በዩኔስኮ ሊመዘገብ መሆኑን ሰሞኑን በዜና መስማቷንና በዓሉ መመዝገብ የሚገባው ትልቅ ቅርስ ነው ብላለች፡፡

ከካናዳ ሞንትሪያ የመጣው ጌተ ማሩዋ በበኩሉ የጥምቀት በዓል በጣም ትልቅ ክብረ በዓል ነውና ያየሁት ነገር አስደንቆኛል ብሏል፡፡

“ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የመጣሁት፤ በደቡብና በሰሜኑ ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ጉብኝት አድርጌያለሁ፤ የተለያየ ባህል አላችሁ፤ የሚያስገርም ነው፤ ካናዳ ውስጥ የተለያዩ ክብረ በዓላት አሉ የኢትዮጵያ ጥምቀት በዓል ግን ይለያል” ነው ያለው፡፡

ማሩዋ በኢትዮጵያ ሲዘዋወር ታታሪና እንግዳ ተቀባይ ህዝብ እንዳየ ጠቅሶ ወደ ካናዳ ሲመለስ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር በህይወት አጋጣሚ አንድ ጊዜ የግዴታ መጎብኘት የሚገባት ሀገር መሆኗን ለካናዳውያን እንደሚናገር አስረድቷል፡፡

በዓሉ በዩኔስኮ ሊመዘገብ መሆኑ እንደሰማና ይህም በጣም ደስ የሚል ዜና ነው ብሏል፡፡

’’ኢትዮጵያ ብዙ ቅርስ ያላት የታደለች ሀገር ናት’’ ያለው ማሩዋ፤ የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

“ሴኔጋልን፣¸ግብጽን፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች ሀገራትን ጎብኝቻለሁ፤ የተለያየ የሚስብ ነገር አላቸው፤ ኢትዮጵያ ግን ከሌሎች ሁሉ የላቀ ባሕል አላት፤ ይህን የተለየ ባህላችሁን ማሥጠበቅ አለባችሁ” ነው ያለው፡፡

የጥምቀት በዓልን ለማየት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባቷን የተናገረችው ጣሊናዊቷ ኢታሊያ በበኩሏ የበዓሉን አስደናቂነት ገልጻለች፡፡

እንደዚህ ዓይነት የመሰል ሃይማኖታዊ በዓል በሌሎች በጎበኘቻቻው ሀገራት እንዳላየችና አስገራሚ እንደሆነባትም ተናግራለች፡፡

በበዓሉና በኢትዮጵያ በሚኖራት ቆይታ ማስታወሻ እየያዘች እንደሆነና ወደ ሀገሯ ስትመለስም ለጓደኞቿ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እሷ ያየችውን እንዲጎበኙ እንደምትነግራቸውም ገልጻለች፡፡

የጥምቀት ክብረ በዓል ከዚህ በላቀ ሆኔታ መተዋወቅና መጠበቅ እንደሚገባውም ኢታሊያ ሳትገልጽ አላለፈችም፡፡

“በዓሉ በዩኔስኮ ሊመዘገብ መሆኑን ስሰማ ተደስቻለሁ፤ እኔም በዓሉ እንዲመዘገብ በማስተዋወቅ በኩል የድርሻዬን እወጣለሁ” ነው ያለችው፡፡

እንደ ኢታሊያ ገለጻ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ከዚህ ቀደም የመጡ ጓደኞቿ ስለ ሀገሪቱ ታሪካዊነት የነገሯትን ሰምታ ነው፡፡