ዶክተር አብይ ላነሷቸው የለውጥ ሃሳቦች ተግባራዊነት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁነን፡- የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች

57
አሶሳ ሚያዝያ 25/2010  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሶሳ ከተማ  ከህዝቡ ጋር በተወያዩበት ወቅት ላነሷቸው የለውጥ ሃሳቦች ተግባራዊነት የድርሻቸውን ለመወጣት   ዝግጁ  መሆናቸውን   ለኢዜአ  የስያታቸውን  የሰጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በክልሉ የሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጧቸው አቅጣጫዎች እውን እንዲሆኑ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ጉደታ ነጋሳ የተባሉ የአሶሳ ነዋሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት የቀረቡላቸውን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ከአካባቢው አመራሮች ጋር በመነጋገር ለመፍታት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን አስታውሰዋል፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ  ያለውን የተፈጥሮ ሃብት የበለጠ በማልማት የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚሆንበትን አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ለክልሉ እድገት መፋጠን ወሳኝነት እንዳለው እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የክልሉ ነባር እና ሌሎችም የሀገሪቱ ብሔሰቦችና ህዝቦች በወንድማማችነት መንፈስ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹበት መንገድ ዘላቂ ሠላም የሚያመጣ ነው "ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት የህዝቡን አንድነት የሚያጠናክር ሃሳብ ማንሳታቸው ተገቢና የሚደግፉት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  ሌለው የከተማው ነዋሪ አቶ ምትኩ ዘነበ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በነፃነት ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብቱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደማይችል  በትኩረት መግለፃቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ እንየው ዘመን የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት የአካባቢው  የተፈጥሮ ሃብት ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲውል ያቀረቡት ሃሳብ ለክልሉ የሰጡትን ትኩረት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ "የክልሉን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ አብሮነትን ማጠናከር እንደሆነ መግለፃቸው አስደስቶኛል" ብለዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተወያዩበት ወቅት በአካባቢያቸው ያነሱትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄያቸውን ለመመለስ ከክልሉ አመራር ጋር እንደሚሰሩ የገለጹትን ሀሳብ በመደገፍ ለተግባራዊኑት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም