ዲፕሎማቶቹ ኢትዮጵያ ካለችበት ለውጥ ጋር የሚጣጣም የዲፕሎማሲ ስራ ለመከወን መክረዋል

97

አዲስ አበባ ጥር 10/2011 ለአምስት ቀናት በተካሄደው የዲፕሎማቶች ውይይት ኢትዮጵያ ካለችበት ለውጥ ጋር የሚጣጣም የዲፕሎማሲ ስራ መከወን የሚያችል ምክክር መካሄዱን ተሳታፊዎች ተናገሩ።

ውይይቱ በውጭ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮችና የዋናውን መስሪያ ቤት ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶች

ተሳትፈውበታል።

በዋናነት በወቅታዊ የኢትዮጵያና የዓለም አዝማሚያ፣ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ትኩረት አድርገውም መክረዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ እንዳሉት የማንኛውም ዲፕሎማሲ አልፋና ኦሜጋ ተግባር ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ለውጥ በዓለማቀፍ መድረክ ሰፊ እድል እንደፈጠረ ጠቁመው ለውጡን በእውቀትና ጥበብ መርቶ ለስትራቴጂካዊ ጥቅም ማዋል ላይ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

ለውጡ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ ማድረጉን ጠቁመው ከእያንዳንዱ ዲፕሎማት ይህንኑ የሚመጥን ስራ 'ይጠበቃል' ብለዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደተለያዩ አገራት በማቅናት ዲያስፖራው ለአገሩ ድጋፍ እንዲያደርግ ሰፊ ስራ መስራታቸውን አውስተዋል።

በዲያስፖራው የተፈጠረውን መነቃቃት እንዴት ወደ አገራዊ ጥቅም መቀየር እንደሚቻል በዲፕሎማቶች ዝርዝር ውይይት መካሄዱንም ገልጸዋል።

በውይይቱ 'በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የሆኑ ተቋማት ተገኝተው ከዲፕሎማቶች ጋር ተቀናጅተው በሚሰሩበት ሁኔታ ተነጋግረዋል' ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም