በሀድያ ዞን በፍትህ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰሩ የፍትህ አካላት ገለጹ

53

ሆሳእና ጥር 10/2011 በሀድያ ዞን በፍትህ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት እንደሚሰሩ የተለያዩ የፍትህ አካላት ገለጹ።

የሀድያ ዞን ፍትህ አካላት በመልካም አስተዳደርና ጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሆሳዕና ከተማ  ውይይት ያዘጋጀው መድረክ ተካሂዷል፡፡

የንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባለሙያ  አቶ አማኑኤል ዳኘው እንደተናገሩት በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ቢኖርም ፖሊስ የጸጥታ ማስከበር ስራውን በተገቢው ሁኔታ እያከናወነ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከተማ የስርቆት ወንጀሎች መበራከታቸው ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ በመክተቱ ፖሊስ የህብረተሰቡን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በተሻለ ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በሃዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል መከላከል የስራ ሂደት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ጸጋዬ ንጉሴ በበኩላቸው በቅንጅታዊ አሰራር ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በፖሊስ በኩል ምርመራ ተደርጎባቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው ወደ ፍርድ ቤት የሚላኩ መዝገቦች በወቅቱ እንደማይታዩ የጠቆሙት አስተባባሪው ፖሊስ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ፈጣን አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

"ችግሮቹ እንዲፈቱም የፍትህ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡

ፍትሃዊ የሆነ የምርመራ ሥራ ባለመሰራቱ ዜጎች ያለአግባብ ለእስራት እየተዳረጉ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የሌሞ ወረዳ ሰላምና ጸጥታ ባለሙያው አቶ መሐመድ ጁሐር ናቸው፡፡

"የፍትህ ተቋማት በቅንጅት ባለመስራታችን ተገልጋዩ ህብረተሰብ ለእንግልት ተዳርጓል" ያሉት ባለሙያው፣ "ችግሮችን ለመፍታት የፍትህ አካለት በቅንጅት መስራት ይኖርብናል" ብለዋል።

የሀድያ ዞን አቃቤ ህግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ገቲሶ ዴታሞ በበኩላቸው የፍትህ አካላት የዞኑን ሰላምና ጸጥታ ማስከበር በህጉ የተሰጣቸው ተግባር በመሆኑ ለችግሮች መፍትሄ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በፍርድ ቤቶች ተገልጋይን ማጉላላት፣ ለውሳኔ የቀረቡ መዝገቦችን ማዘግየት፣ ህጻናትን ይዘው ለሚመጡ ባለ ጉዳዮች ቅድሚያ አለመስጠት፣ የህዝቡን ጥቅም አለማስቀደም፣ ልማዳዊ አሰራርን መከተል፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በአግባቡ አለመቆጣጠርና ማስረጃ ሳይኖር ሰዎችን ማሰር በመድረኩ ከተነሱ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ  ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም