የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ ለሰላም መቆም አለባቸው…ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ አብርሃም

403

ባህርዳር ጥር10/2011 “የኦርቶዶክስ ምዕመናን እንደ ሀገር የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖራችሁ ለአንዲት ሀገራችሁ እድገትና ሰላም ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋራ  በጋራ በመሆን ለሰላም ዘብ መቆም ይጠበቅባችኋል” ሲሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ብፁዕ አቡነ አብረሃም ገለጹ።

በአማራ ክልል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የከተራ በዓል በሰላማዊ ሁኔታ ማምሻውን ተካሄዷል።

በባህር ዳር ከተማ በተከበረው የከተራ በዓል ላይ ብፁዕ አቡነ አብረሃም እንደገለፁት ሃይማኖት የግል አገር የጋራ ስለሆነች ምዕመናን የራሳቸውን እምነት አጥብቀው በመያዝ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ወንድማማችነታቸውን አጠናክረው ለሃገር ሰላም ሊሰሩ ይገባል።

“ዛሬ ባህሏና እምነቷ ሳይበረዝ አባቶች ጠብቀው ያቆዩዋት የአፍሪካ ኩራት የሆነች ኢትዮጵያን ለመረከብ የተቻለው ኢትዮጵያዊያን ቀደምት አባቶች የእምነትና የዘር ልዩነት ሳይገድባቸው የደም ዋጋ ስለከፈሉ ነው”ብለዋል።

“ዛሬ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ሃይማኖትንና ማንነትን መሰረት በማድረግ  ሀገርን አደጋ ላይ  ለመጣል እየተሰራ ስለሆነ ምዕመናን ይህንን ቀድመው በማወቅ ሊዋጉት ይገባል”ብለዋል። 

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ  አቶ ሙሉቀን አየሁ በበኩላቸው የተለያዩ ማንነቶች  መናኸሪያ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያደረገችውን ትልቅ አስተዋጽኦ በማጠናከር ምዕመናን በልዩነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን እንዲያዳብሩ መስራት እንደሚገባት ጠቅሰዋል።

የበዓሉ ታዳሚ አቶ ስለሺ የኔው ለበዓሉ መከበር ወጣቱ የተለየ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው “በዓሉ በስላም እንደተጀመረ በሰላም እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንሰራለን” ብለዋል።

የከተራ በዓል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የከተማው ወጣቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን በበዓሉ ላይም የውጭ ሃገራት ቱሪስቶችን ጨመሮ የከተማው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።              

በዓሉ በተመሳሳይ በጎንደር፣ በወልዲያ፣ በደሴ በደብረ ብርሃንና በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ማሽሻውን መከበሩን ለማረጋገጥ ተችሏል።