ምክር ቤቱ ለስፖርቱ ዘርፍ ማጠናከሪያ 8 ሚሊዮን 800ሺህ ብር በጀት አጸደቀ

96

ሶዶ ጥር 10/2011 የወላይታ ዞን ስፖርት ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጉባኤ የስፖርቱን ዘርፍ ለማጠናከር የሚያግዝ 8 ሚሊዮን  800ሺህ ብር በጀት አጸደቀ፡፡

የስፖርት የምክር ቤት ሰብሳቢ ተወካይና የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሬው ሞገስ እንደተናገሩት በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ከፍ እያለ የመጣውን የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማሳደግና በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ዘንድሮ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡

ለዚህ ምክር ቤቱ ባጸደቀው በጀት በዞኑ ሁሉም መዋቅሮች የስፖርት ማዘውተሪያና መዝናኛ ስፍራዎች ማመቻቸት፣ ነባር ስታዲየሞች ጥገናና የስፖርታዊ ጨዋነት ስልጠናዎች ይካሄዳል፡

እንዲሁም የታዳጊዎችን ተሳትፎ በማሳደግ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተተኪዎች ለማፍራት ፕሮጄክቶችና የባህል ስፖርቶች ማጠናከር ሌላው ተግባር ነው፡፡

በተለያየ መልኩ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ለመመለስ ባለሃብቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ ለማሳተፍም የተለያዩ ተግባራት ተጀምሯል፡፡

የነበረውን አቅም በተለያዩ ስልጠናዎችና አቅርቦቶች ማጎልበት  ተሳታፊነትንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውና ይህንን በተቀናጀ መልኩ መመራት መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት የስፖርት ዘርፍ አስተባባሪ  አቶ ኢያሱ ነጋ ናቸው፡፡

በዚህ መነሻም እግር ኳስ ፣ ቦሊቦል ፣ አትሌቲክስ ፣ ቅርጫት ኳስና  ጠረጴዛ ቴኒስ በ183 ቀበሌዎች የስፖርት ምክር ቤቶችና ማህበራትን በማደራጀት የሙያ ስልጠና፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የስፖርት ምክር ቤቱ አባል  አቶ መርሁን መንገሻ በበከላቸው በዞኑ በስፖርቱ ዘርፍ የህዝቡ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ ቢመጣም ከፍላጎት አንጻር ሊሰራ  እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

"በስፖርት ተሳትፎ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጤናማና ምርታማ ዜጋን ለማፍራትም ያለው ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም አቅማችንን አሟጠን ለመጠቀምም መስራት ይገባናል" ብለዋል፡፡

በአካባቢው በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የስራ ዕድል ፈጠራ እየሆኑ መምጣታቸውንና በተገቢው ቢሰራበት የተሻለ ውጤት ሊመዘገብባቸው እንደሚችል የሶዶ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኡኩሞ ተናግረዋል፡፡

ከማዘውተሪያ አንጻር በሶዶ በተያዘው ዓመት  ብቻ ከ16 በላይ ቦታዎች ምቹ እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

የስፖርት ምክር ቤቱ ጉባኤ ከማጠናከሪያው በጀቱ ሌላ  የ2010 በጀት ዓመት የዘርፉ አፈጸጸም በመገምገምና የተያዘውን የስራ ዘመን ዕቅድ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም