በደቡብ ክልል ጥገኛ የአንጀት ትላትሎችና ቢሊሀርዚያን ለመከላከል በትምህርት ቤቶች መድኃኒት እየታደለ ነው

88

ሀዋሳ  ጥር 10/5/2011 በደቡብ ክልል በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 14 ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎች ጥገኛ የአንጀት ትላትሎችና ቢልሀርዚያን መከላከል የሚያስችል እንክብል በዘመቻ እየታደለ መሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

መድኃኒቱን የወሰዱ አንዳንድ ተማሪዎች የሆድ ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽና ራስን መሳት ቢከሰትባቸውም ምንም ጉዳት እንደማያመጣም ቢሮው አመልክቷል።

በቢሮው የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ዋና የሥራ ሂደት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ታደለ ለኢዜአ እንዳሉት በተለይ በታዳጊዎችና በወጣቶች ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር እያስከተለ ያለውን ጥገኛ የአንጀት ትላትል ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት እደላ እየተካሄደ ነው።

ከትምህርት ሚንስቴር ጋር በመቀናጀት ከጥር 7 እስከ 13 ቀን 2011 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው የመድኃኒት እደላ ዘመቻ ቁጥራቸው ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።

የአንጀት ጥገኛ ትላትሎችና ቢልሀርዚያ በሽታ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የአንጀት መታጠፍና ካንሰርን ሊያስከትሉ እንደሚችሉና በተለይ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ለሚከሰተው የመቀንጨር ችግር ምክንያት እንደሚሆንም አስረድተዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 14 ዓመት ለሆኑ ህጻናት በሚማሩበት ትምህርት ቤት የመድኃኒት እደላው መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

አቶ ታፈሰ እንዳሉት የመድኃኒት እደላው በሚካሄድባቸው አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተወሰኑ ተማሪዎች ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽና አልፎ አልፎ ራስን የመሳት ሁኔታዎች ታይቶባቸዋል።

ይህ የመድኃኒቱ ባህሪ መሆኑን ገልጸው፣ ተማሪዎች በተለይ ቁርስ ሳይበሉ መድኃኒቱን ሲወስዱ ችግሩ እንደሚከሰትባቸው የማስገነዝብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀድራላህ አህመድ በበኩላቸው እንዳሉት የአንጀት ትላትልና የቢልሀርዚያ መድኃኒት እደላው በዘመቻ እየተካሄደ ያለው ከጤና ጥበቃ ሚንስቴርና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።

ጥገኛ የአንጀት ትላትልና ቢልሀርዚያ በተለይ በታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ ከሚያስከትሉት የጤና ችግር ባለፈ በትምህርት አቀባበላቸው የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው መድኃኒቱን በትክክል እንዲወስዱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም