በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ ሞዴል አርሶ አደሮች በዓመት እስከ 1ዐዐ ሺህ ብር ገቢ እያገኙ ነው

56

ፍቼ ጥር 10/2011 በምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ ሞዴል አርሶ አደሮች በዓመት እስከ 1ዐዐ ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞዴል አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ 

በዞኑ አምስት ወረዳዎች ለሚገኙ 1 ሺህ 577 ሞዴል አርሶ አደሮች የሽንብራና የግብስ ምርጥ ዘር አምርተው የመሸጥ እውቅና መሰጠቱን ዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት  ኑሮቸውን እያሻሻሉ ያሉት ስንዴ፣ ሽንብራ እና ለቢራ ብቅል የሚሆን ገብስ እያመረቱ ለቢፍቱ ሰላሌ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ነው፡፡

ከወረዳው ሞዴል አርሶ አደሮች መካከል በግራር ጃርሶ የቶርባን አሼ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ  ጌቱ ሰኚ ሲሆኑ ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በአንድ ተኩል  ሄክታር መሬታቸው ላይ ያገኙትን 38 ኩንታል ምርጥ የሽንብራ ዘር በመሸጥ ተጠቃሚ እንደሆኑ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

ኩንታሉን  የሽንብራ ምርጥ ዘር እስከ 2 ሺ 5ዐዐ ብር ለዩኒየን በማቅረብ  ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየዘመኑ እስከ 1ዐዐሺ ብር የሚደርስ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ልጆቻቸውን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከፍለው ከማስተማር በተጨማሪ በአካባቢያቸው የእህል ወፍጮ አቋቁመው ኑሮቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው አስታውቀዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ኃይሉ ኩምሳ በበኩላቸው  ከመደበኛ እርሻ በተጓዳኝ ለቢራ ብቅል የሚውል ገብስ የማባዛት ሥራ ላይ ከተሰማራ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ከንታሉን የቢራ ገብስ እስከ 1ሺህ 8ዐዐ ብር በመሸጥ ጥሩ ገቢ ማግኘታቸው አስረድተዋል ።

በወረዳው የወርጡ ቀበሌ ምርጥ የስንዴ ዘር አምራች አቶ በቀለ ወርዶፋ እነዳሉት ደግሞ  ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጥ የስንዴ ዘር በማባዛት እስከ 65 ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ ማግኘት ችለዋል፡፡

ባገኙት ገቢም የመኖሪያ ቤታቸውን የውስጥ ቁሳቁስ ዘመናዊ በማድረግ ህይወታቸውን ከቀድሞ በተሻለ ሁኔታ እንደለወጡ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ አምስት ወረዳዎች የሚገኙ 1ሺህ 577 ታታሪና ሞዴል አርሶ አደሮች በባለፈው ዓመትና በዘንድሮ የምርት ዘመን 2 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ 41 ሺህ ኩንታል የስንዴ፣ የሽንብራና የግብስ ምርጥ ዘር አምርተው የመሸጥ እውቅና እንደተሰጣቸው የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የግብዓት  ፈፃሚ አቶ በላይ ደረጄ  ካለፈው ዓመት ጀምሮ እውቅና ያገኙት አርሶ አደሮች በግራር ጃርሶ ፣ኩዩ ፣ ደገም፣ ሂደቡ አቦቴ እና ጅዳ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ እውቅናውን ያገኙት ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅትና ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር ላለፉት አምስት ዓመታት በሰርቶ ማሳያዎች በጋራ  በመስራታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ በባለሙያዎችና በተመራማሪዎች በሚሰጣቸው ሙያዊ ድጋፍና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመታገዝ በሄክታር ስንዴና ገብስ ከ5ዐ እስከ 55 ኩንታል ሽንብራ ደግሞ 4ዐ ኩንታል እንደሚያገኙ አመልክተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም