ኢትዮጵያዊያን በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይገደቡ በኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ሊስተናገዱ ይገባል

76

አዲስ አበባ ጥር 10/2011 ኢትዮጵያዊያን በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይገደቡ በአገሪቱ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲስተናገዱ በሮች ክፍት ሊሆኑ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አሳሰቡ።

ኢትዮጵያ በቀጣናውና በገልፍ አገራት የምትታወቅበትን የአስታራቂነት ሚና በማስቀጠል ረገድ ዲፕሎማቶች ሚናቸውን አንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በውጭ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮችና የዋናውን መስሪያ ቤት ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶቸ ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ዛሬ ተጠናቋል።

በመላው ዓለም ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያዊያን ምንም አይነት የፖለቲካ አመለካካት ቢኖራቸው በኤምባሲዎች፣ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችና ሚሲዮኖች እንደ ቤታቸው ሊስተናገዱ ይገባል" ብለዋል

ይህን በማድረግ ዲያስፖራውን በአገሩ ልማት ተሳታፊ ከማድረግ ባለፈ 'ስለ አገሩ የሚናገርና ለአገሩ ጥቅም የሚከራከር ዜጋ ማድረግ ይቻላል' ነው ያሉት።

ዲፕሎማቶች በዲያስፖራውና በመንግስት መካከል የነበረው የጥላቻ ግድግዳ ፈርሶ እየተገነባ ባለው የፍቅር ድልድይ ላይ የግንበኝነት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተያያዘ ዜና ዶክተር ወርቅነህ ኢትዮጵያ በኢጋድ አገራት መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር አበክራ እንደምትሰራ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለዲፕሎማሲ ጥቅም ማዋል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በገልፍ አገራት መካካል በተፈጠረው ክፍፍል ያላትን የገለልተኝነት ቦታ ይዛ አንደምትቀጥልም አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው የተፈጠረው ውጥረት በሰላም አንዲፈታ ያላትን ብርቱ አቋም በመጠቆም።

ዲፕሎማቶቹ በውይይታቸው መክፈቻ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር "ዓለም ዓቀፍ አዝማሚያዎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ" በሚል ርዕስ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም