በምዕራብ ጎንደር ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ መሰጠት ተጀመረ

40

ጎንደር ጥር 10/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰሞኑን በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ መሰጠት መጀመሩን የዞኑ ማህበራዊ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

ለተፈናቃዮች ከትላንት ጀምሮ የምግብና የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት የሰብአዊ ደጋፉ ማቅረብ   የጀመረው በገንዳ ውሀ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ 250 ተፈናቃዮች ነው።

ከአማራ ክልል አደጋ መከላከል ቢሮ የተገኘ 441 ኩንታል ስንዴና አልሚ ምግብ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል ።

አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮችም ከባህርዳር በመጡ የህክምና ቡድን አባላት አማካኝነት እርዳታ የተደረገላቸው ይገኛል።

"በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ለወገኖቹ እሰካሁን ድጋፍ ሳይደረግ ቆይቷል"  ያሉት ኃላፊው አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ ድጋፉ መቅረብ መጀመሩን ተናግረዋል ።

ሰብዓዊ እርዳታው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  አመላክተዋል ።

በገንዳውሃ ከተማ መከላከያ ካምፕ ተጠልለው ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ ዘባደር ተረፈ "የዘገየም ቢሆን የእርዳታው መጀመር መንግስት ከጎናችን ስለመሆኑ እንድንገነዘብ አድርጎናል " ብለዋል።

"ብርድ ልብስና ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችም በፍጥነት ሊቀርቡልን ይገባል" ሲሉም ጠቁመዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ለህፃናት የዕለት ምግብ በማቅረብ  እያደረጉላቸው ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ።

"የተጀመረው የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ያለው ለቆሰሉ ተፈናቃዮች ብቻ ነው" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፍቅርተ አያሌው ናቸው ።

በሌላ የጤና መታወክ  ላጋጠማቸው በጊዜያዊ መጠለያው አገልግሎቱ ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

መንግስት የአካባቢውን ሰላም በመመለስ አስተማማኝ የኑሮ ዋስትና እንድናገኝ ሊያደርግ ይገባል" ሲሉ ወይዘሮ ፍቅርተ ጠይቀዋል ።

በዞኑ በነበረው የፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው  የተፈናቀሉ 4ሺህ 800  ወገኖች እንደሚገኙ ከዞኑ ማህበራዊ ልማት መምሪያ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም