ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያየ

1466

አዲስ አበባ ጥር 10/2011 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ራሱን ችሎ እንዲቋቋም በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች  ከተቋሙ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ።

የምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተቋሙ ደንቦች ላይ ያሉ እጥረቶች፣ የስያሜ ለውጥ፣ የስራ አስፈጻሚና የቦርድ አባላት አወቃቀር፣ የሰራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፣ የበጀትና የገቢ ምንጮችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች አንስተዋል።

የተቋሙን በጀትና የገቢ ምንጭ በተመለከተም በምን መልኩ ማስኬድ እንደሚገባ አስተያየቶች ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስያሜ መቀየር የለበትም የሚል ሀሳብም ተሰንዝሯል።

የተቋሙን የስራ አመራር ቦርድ ከስራው ጋር ተገቢነት ባለው መልኩ ማዋቀር እንደሚገባም አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችም ያለውን የሰው ኃይል፣ የግብዓትና ሌሎች ችግሮች ለመፍታትና የተቋቋመበትን ዓላማ በማሳካት ረገድ ውጤታማ እንዲሆን አዋጁን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በቀለ ሙለታ ተቋሙ ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ዜናና ፕሮግራሞችን ከማቅረብ ባለፈ በወቅታዊ ጉዳዮች ይዘቶችን አዘጋጅቶ የማቅረብ፣ የህዝብ አስተያየት ጥናትና ሌሎች የገቢ ማስገኛዎች መስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ተቋሙ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማሟላት ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ሊኖረው ስለሚገባ የቦርዱን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የመወሰን ስልጣን የማሻሻል አስፈላጊነት አብራርተዋል።

የተቋሙን ስያሜ በተመለከተም የእንግሊዝኛው ስያሜ ሳይቀየር በአማርኛ “የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት” በሚል እንዲሆን በተቋሙ በኩል ሀሳብ መኖሩን ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን ከተቋሙ ኃላፊዎች የተነሱ ሀሳቦች በጽሁፍ እንዲቀርቡና ኮሚቴውም ይህንኑ መሰረት በማድረግ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።