የጎባ ካቶሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራ መስተጓጎል አሳስቦናል… ወላጆች

1221

ጎባ ጥር 10/2011 በባሌ ዞን ጎባ ከተማ የሚገኘው የካቶሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የሁለት ወር ደመወዝ ሳይከፈላቸው በመቅረቱ መቸገራቸውን ገለጹ፡፡

የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ልጆቻቸው በአጉል ሰዓት እንዳይበተኑባቸው  ስጋታቸውን ገልጸዋል።

መምህርት አለሚቱ ቱፋ እንደተናገሩት ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ወርሃዊ ደመወዛቸው ባልታወቀ ምክንያት ተቋርጦባቸዋል ።

በዚህም የተነሳ ቤተሰባቸውን በአግባቡ ለማስተዳደር ከመቸገራቸውም ባሻገር የማስተማር ተነሳሽነታቸው ጫና ስለፈጠረባቸው የሚመለከታቸው አካላት መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል ።

“ከትምህርት ቤቱ ጋር በገባነው ውል መሰረት መደበኛ ስራችን ላይ እያለን ደመወዛችን መቋረጡ አግባብነት ስለሌለው ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እልባት እንዲሰጠን እንጠይቃለን” ያሉት ደግሞ ሌላው የትምህርት ቤቱ መምህር አሳዬ ተስፋዬ ናቸው፡፡

የሌሎቹን መምህራን የቅሬታ ሀሳብ እንደሚጋሩ የገለጹት መምህር አብዱልቃድር ማህሙድም ደግሞ “ቤተሰባችንን የምናስተዳድርበት ሌላ የገቢ ምንጭ ስለሌን በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ ምላሽ እንዲሰጡን እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡

አስተያየት ሰጪ መምህራኑ እንዳሉት ከክፍያም ባሻገር የተማሪዎችና የትምህርት ቤቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ስለሚያሳስባቸው በአፋጣኝ እልባት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።  

ከተማሪ ወላጆች መካከል አቶ ሱፊ ሎሌ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቱ አቅም የሌላቸው ቤተሰቦችን ለመርዳት የተቋቋመ ቢሆንም ለሁለት ልጆቻቸው የሚጠየቁት እየከበዳቸው መጥቷል።

“በትምህርት ቤቱ የተጠየቅነውን ክፍያ ብንፈጽምም ትምህርት ቤቱ ለመምህራኑ የሚከፍለውን ደመወዝ በማቋረጡ ልጆቻችን ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ስጋት አድሮብናል” ብለዋል ።

“ቀደም ሲል የመክፈል አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች በተመጣጣኝ ዋጋ የትምህርት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ትምህርት ቤት በየዓመቱ አቅማችንን ያላገናዘበ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ አግባብ አይደለም ” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አስቴር ከተማ  ናቸው።

እንደዚህም ሆኖ አሁን ላይ የትምህርት መቋረጥ እንዳይከሰት የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረት ሊያደርጉበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ትምህርት ቤቱ ለመምህራን ደመወዝ ከፍሎ ማስተማር ካልቻለ የአስተዳደር ስራውን ለመንግስት እንዲያስተላልፍ ጠይቀዋል ፡፡

የባሌ ሮቤና አካባቢዋ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ጸኃፊ አቶ ፈይሳ ገመዳ ስለሁኔታው ተጠይቀው  ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሲደረግለት የነበረው ድጋፍ በመቋረጡ ለመምህራንና ሰራቶኞች ደመወዝ ለመክፈል መቸገሩን ተናግረዋል ።

ከማህበረሰቡ ጋር ውይይትና መግባባት ላይ ሳይደረስ በወርሃዊ የትምህርት ክፍያ ላይ ጭማሪ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ ያመኑት ጸኃፊው “እንደዚያም  ሆኖ ግን የተማሪ ወላጆች እየፈጸሙ የሚገኙት ክፍያ የመምህራን ደመወዝ የሚሸፍን አይደለም”ብለዋል ።

ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር በተገባው ውል መሰረት የመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ደመወዝ እንደሚከፈልና ስለትምህርት ቤቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከተማሪ ወላጆችና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ተጨማሪ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳ ግዛው በበኩላቸው የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለማህበረሰቡ ከምትሰጣቸው ማህበራዊ  አገልግሎቶች ትምህርት አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል

“ከመምህራን የደመወዝ ክፍያና የትምህርት ቤቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ጋር በተያያዘ እየተነሳ ያለውን ቅሬታ ለማጣራት ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል”ያሉት ኃላፊው ችግሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በባሌ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡