ወጣቶቹ የከተራና የጥምቀት በዓላትን በሰላማዊ መንገድ ለማክበር ተዘጋጅተናል --የድሬዳዋ ከተማ ወጣቶች

59

ድሬዳዋ ጥር 10/2011 የድሬዳዋ ከተማ ወጣቶች የከተራና የጥምቀት በዓላትን በሰላማዊ መንገድ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገለጹ።

በከተማው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡት ወጣቶች እንዳስታወቁት የሃይማኖት ልዩነት ሳይወስናቸው በዓላቱን በሰላም ለማክበር ተዘጋጅተዋል፡፡

ዓለምነህ መኮንንና ጓደኛው እስክንድር መሐመድ በሳቢያን ገብርኤል አካባቢ በዓላቱን ሰላማዊነታቸውን ጠብቀው ለማክበር ከተዘጋጁ ወጣቶች መካከል ናቸው። እነዚህን ዘመናት ያስቆጠሩ በዓላት ያለ እምነት ልዩነት በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ይገልጻሉ፡፡

''እኔና አለምነህ ብቻ ሳንሆን፤ የአካባቢው ወጣት ኃይማኖታዊ በዓላት ወቅት በዓላት ያማሩና የደመቁ ለማድረግ እንሰራለን'' በማለትም የሃይማኖት ልዩነት አንድነትን እንደማያሳጣ የሚናገረው እስክንድር ነው።

ተመሣሣይ ሃሳብን ያንፀባረቀው የገንደ ቆሬ ሰፈር የሚኖረው ወጣት ኤርሚያስ አየለ ወጣቶቹ ተቀናጅተው በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

''በሁሉም ነገር የተሳሰረው ማንነታችንና ኅብረታችንን በማጠናከር የአካባቢያችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሰራን ነው'' ያለው ደግሞ ወጣት ነቢል ከማል ነው፡፡ 

የከዚራ ሠፈር ነዋሪዋ ወጣት ሰላም ኤፍሬም ''ወጣቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የመጣው ለውጥ በድሬዳዋም ይበልጥ እንዲያብብ እየሰራ ይገኛል'' ብላለች፡፡

በተለይ በከተማው አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶች እንዲቆሙና በውይይት እንዲፈቱ በዓላቱ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥሩ እምነቷን ገልጻለች፡፡

ተመሳሳይ ሃሳብን ያንፀባረቀው የከዚራ ነዋሪ ወጣት ኢዩኤል ሙሉጌታ በበኩሉ በዓሉ በሰላም እንዲከበር በአካባቢያቸው የሚገኙ የሁለቱም ኃይማኖት ተከታይ ወጣቶች ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸው ገልጿል።

በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ በጋራ ተሰባስበን መስራቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር አጋጣሚ ይፈጥራል ያለው ደግሞ ወጣት አብዱልአዚዝ ሱሌይማን ነው፡፡

ወጣቱ በሁሉም በዓላት ወቅት ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብሏል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ቡድን መሪ ዋና ሳጅን ባንተዓለም ግርማ ወጣቶቹ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በዓላቱን  በሰላም ለማክበር እያደረጉት ያለው ጥረት  አበረታች  መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፀሐፊ ኡስታዝ ኢዮብ ሐሰን ''የድሬዳዋ ሕዝብ በኅዘንና በደስታ የማይለያይ፤ በልዩነት ውስጥ አንድነቱ የጠነከረ ማህበረሰብ የመሆኑ እውነታ በነዚህ በዓላት ወቅት ይበልጥ ይንፀባረቃል'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ ተቀናጅተው ሰላምን ለማስከበርና በዓላቱን ለማድመቅ የሚያከናውኗቸው ተግባራት አስደሳች ናቸው ብለዋል።

ለመላው የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆንም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መልዓከ ህይወት አባገብረማርያም ሥነ-ፀሀይ የቅዱስ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በበኩላቸው ወጣቶቹ ያለምንም የእምነት ልዩነት በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዳስደስታቸው ይገልጻሉ፡፡

የአስተዳደሩ የእስልምና ጉዳዮች  ምክር ቤት በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ ቁሳቁስ መደገፉን አስታውቀዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በከተማዋ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች ወጣቶች  ተደራጅተው አካባቢያቸውን እያስዋቡና ለታቦታቱ መሄጃ ምንጣፍ ሲያነጥፉ  ተመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ በአዳባባይ ከሚከበሩ የሃይማኖት በዓላት የሚጠቀሱት የከተራና የጥምቀት በዓላት ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ የጥምቀት በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)በቅርስነት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም