የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታ ለማበረታታት የተገነቡት አምስት የሳይንስ ካፌዎች አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም

141

አዲስ አበባ ጥር 10/2011 የወጣቶችን የፈጠራ ችሎታ ለማበረታታት በአዲስ አበባ የተገነቡ አምስት የሳይንስ ካፌዎች በግብዓት አለመሟላት አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ተባለ።

ወጣቶች የአገሪቱን የቴክኖሎጂ አመራርነት እንዲረከቡ ለማስቻል በቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን ያካተቱ የሳይንስ ካፌዎች መገንባታቸው ይታወቃል።

ስራው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የወጣት ማዕከላትን በመጠቀምና የዲዛይን ለውጥ በማድረግ ኮምፒዩተርና ቴሌቪዥኖችን ጨምሮ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማደራጀትን ያካትታል።

እያንዳንዳቸው ከ4 እስከ 6 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በአምስት የወጣቶች ማዕከላት ውስጥ ተገንብተው ከአንድ ዓመት በፊት የተመረቁት የሳይንስ ካፌዎች አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ የወጣት ማዕከላቱ ሰራተኞች ለኢዜአ ተናግረዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 5 ወጣት ማዕከል ቤተ መፃሐፍት ባለሙያዋ ወይዘሮ እታገኝ ሙላት ቤተ-መፃህፍቱን ለአገልግሎቱ ዝግጁ ለማድረግ ከአንድ ዓመት በላይ በእድሳት ላይ መቆየቱን ገልጸዋል።

ከወራት በፊት እድሳቱ ተጠናቆ የቀድሞውን አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም የሳይንስ ካፌው ስራ እንዳይጀምር የኮምፒዩተር አለመኖር ችግር እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ወጣት ማዕከል ሰራተኛ አቶ ብርሃኑ ወዳጆም የወጣት ማዕከሉ ከግንባታው መጠናቀቅ በዘለለ በተባሉት ቁሳቁሶች አለመደራጀቱን ነው ያስረዱት።

ሳይንስ ካፌውን ወደ ስራ ለማስገባት ኮምፒዩተሮችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ሊሟሉ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጣቶች ማብቃትና ተጠቃሚነት ዳይሬክቶሬት በበኩሉ ከቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በግንቦት 2009 ዓ.ም የተዋዋለው የሳይንስ ካፌዎቹ ግንባታ በሶስት ወራት እንዲጠናቀቅ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዳይሬክቶሬቱ የወጣት ማካተትና አገልግሎት ማስፋት ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ጤናዬ ታምሩ እንደተናገሩት የቀድሞው ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአሁኑ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኮምፒዩተሮች እንዲያስረክባቸውና ባለሙያዎችን እንዲያሰለጥንላቸው ጠይቀዋል።

ቢሮው የሰራተኞች ምልመላ አጠናቆ የግብዓት መሟላት እየተጠባበቀ መሆኑንም አክለዋል።

በመዲናዋ የተገነቡት አምስቱ የሳይንስ ካፌዎች ለምረቃ የበቁት ህዳር 2010 ዓ.ም ነው። 

ኢዜአ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም