በዞኑ ኤች አይ ቪ በደማቸው የተገኘባቸው ወገኖች መድኃኒት እንዲጀምሩ ተደረገ

90

አምቦ  ጥር 10/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የደም ምርመራ አካሄደው ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ወገኖች በሙሉ መድኃኒት መውሰድ እንዲጀምሩ መደረጉን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ፍሌ ነሜ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት 49 ሺህ 392 ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የደም ምርመራ አድርገዋል።

ከተመረመሩት ውስጥ 344 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘ ሲሆን ወዲያውኑም የፀረ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ መድኃኒት እንዲወስዱ መደረጉን አስተባባሪው ተናግረዋል።

በቅድመ መከላከል ሥራውም በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ለ152 ሺህ 600 ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን ነው ያስረዱት።

አስተባባሪው እንዳሉት የደም ምርመራ አገልግሎቱ የተሰጠው በዞኑ በሚገኙ ሰባት ሆስፒታሎችና 22 ጤና ጣቢያዎች አማካኝነት ነው።

"ቢፍቱ" የተባለ ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ማህበር ሊቀመንበር  አቶ ጌቱ አበራ በበኩላቸው ማህበሩ ከ200 በላይ አባላቱን አሰማርቶ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራቱን ገልፀዋል ።

የጸረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት መውሰድ የጀመሩ የማህበሩ አባላትም መድኃኒታቸውን በአግባቡ እንዲወስዱ ማህበሩ ቤት ለቤት በመሄድ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የደም ምርመራ ከማድረጋቸው በፊት በሳምባ በሽታ ታመው በአልጋ ላይ ውለው እንደነበር የገለጹት ደግሞ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ምንትዋብ ፈይሳ ናቸው።

" ምርመራ አድርጌ ቫይረሱ በደሜ እንዳለ ሳውቅ ወዲያውኑ የጸረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት በመጀመሬ ጤናዬ ተመልሶ በአሁኑ ወቅት ሰርቼ ቤተሰቤን በማስተዳዳር ላይ እገኛለው " ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በምርመራ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለባቸው ማወቃቸው ቀጣይ ሕይወታቸውን ለማስተካከል እንደጠቀማቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ፍቃዱ ቡልቶ የተባሉ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡

በጤና ባለሙያ ምክር ታግዘው ጤንነታቸውን መጠበቃቸው ከሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ነጻ እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

"በአሁኑ ወቅት በአምቦ ሆስፒታል የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሕሙማንን በመንከባከብና ምክር በመስጠት እያገለገልኩ እገኛለሁ" ብለዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት በተያዘው የበጀት ዓመት 126 ሺህ 136 ለሚሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይ ቪ የምክርና የደም ምርመራ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ታውቋል።

ተመረምረው ቫይረሱ ከተገኘባቸው ወገኖች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ወዲያውኑ መድኃኒት መጀመር አለባቸው የሚለው ከሦስቱ 90ዎች መርህ አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም