የጥምቀት በዓል ሁሉንም በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብ ነው

102

                 

ጥር 9/2011 ከስድስት ኪሎ ወደ ጃል ሜዳ በሚወስደው መንገድና አደባባይ ላይ ወጣቶች ለበዓሉ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን  ቅኝት አድርገናል፡፡

በዝግጅቱ የእስልምና እምነት ተከታዮችም ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡

ከዝግጅቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ጀሚል ሰይድ ክርስቲያን ወንድሞቹ በአሉን በደስታ እንዲያከብሩ የሚያደርጉትን ዝግጅት እያገዘ እንደሆነ ነው የነገረን።  

ጀሚል እንደሚለው ከበዓሉ እለት ጀምሮ እስከ ፍጸሜው ድረስ ድጋፍ እያደረገ በአሉን አብሮ በደስታ ያከብራል፡፡

በበዓሉን አብሮ ለማክበር በእለቱ የሚለብሰው ቲሸርት እደተዘጋጀለትም ተናግሯል፡፡

በዓሉን ከሙስሊም አብሮ አደግ ወንድሞቹ ጋር አብሮ እንደሚያከብር የተናገረው የዝግጅቱ  ተሳታፊ በከሪያን ሃይለእየሱስ በበኩሉ “ለበዓሉ በምናደርገው ዝግጅት አደባባይ ከማስዋብ ጀምሮ በመንገድ ጠረጋም እያገዙን ነው” ብሏል።   

“በዓሉ ግጭቶችንና ቅራኔዎችን እንድንረሳና አዲስ መንፈስ እንድላበስ ስለሚያደረግ  በሁሉም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሠጠው ነው” ብሏል፡፡

ጥምቀት የአደባባይ በዓል በመሆኑ የተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚስተናገዱበት እለት ነው ያለው ወጣት በከሪያን ከሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ባለፈ የተለያዩ ብሄር፣ብሄረሰቦች ባህለዊ ጭፈራዎችና የባህል አልባሳት የሚያሸበርቁበት ነው ይላል።  

ልጃ ገረዶችና ወይዛዝርቶች በባህል ልብሶች ተውበው የሚታዩበት እለት በመሆኑም ከባህላዊው የሎሚ ውርወራ ጀምሮ እስከ መተጫጨት መልካም አጋጣሚ የሚፈጠርበት እለት መሆኑም ነግሮናል፡፡

ከአመታት በፊት በዓሉን ለማክር በሚደረገው ሂደት አለመግባባት ይከሰት እንደነበር ያስታወሰው ወጣቱ አሁን ላይ ሁሉም ተስማምቶ በአንድነት የሚከብርበት እድል ተፈጥሯል ይላል።

በበዓሉ እለት በጃል ሜዳ የሚደረጉ ልዩ ልዩ ባህላዊ ትዕእንቶች ከአእምሮው የማይጠፉ ትዝታዎች ጥለው እንደሚያልፉ የሚናገረው ደግሞ ወጣት ፍቅረስላሴ ያረጋል ነው፡፡

በጥምቀት በዓል የምናሳየውን ፍቅርና አንድነት በእለት ተእለት ተግባራችን ልናዳብረው ይገባል ያለው ደግሞ  ወጣት ነው፡፡

በአልን በደስታ ማክበር የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው ያለው ፍቅረስላሴ “እኛ ወጣቶች ትዕግስተኛ በመሆንና ቆም ብለን በማስተዋል የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት የበኩላችን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርብናል” ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም