በዩኒቨርሲቲው ነጻ የሕግ አገልግሎት መጠቀማቸውን የኢንጭኒና የአምቦ ከተሞች ችግረኛ ሴቶችና አረጋውያን ገለጹ

53

አምቦ ጥር10/2011 የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው ነጻ የሕግ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን የኢንጭኒና የአምቦ ከተሞች ችግረኛ ሴቶችና አረጋውያን ገለጹ፡፡       

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ለ2ሺህ 675 ተጠቂ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህግ አገልግሎት መስጠቱን ገልጿል፡፡ 

በምዕራብ ሸዋ ዞን የኢንጭኒ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ አረጋሽ ፊጡማ ለኢዜአ እንደገለጹት ከባለቤታቸው ጋር በነበራቸው የንብረት ክርክር  በአቅም ማነስ ምክንያት ለረጅም ጊዜያት ወደ ፍርድ ቤት ሳይሄዱ ቆይተዋል፡፡    

ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ጉዳያቸው በህግ ባለሙያ ተይዞ ስለተከራረላቸው ፍትህ አግኝቻለሁ ብለዋል፡፡    

በውጤቱም ሁለት ሄክታር የእርሻ መሬትና 400 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ ከባለቤታቸው ጋር መካፈላቸውን ተናግረዋል፡፡ 

"ዩኒቨርሲቲው ለእኔ አባት ነው የሆነኝ፣ ጉዳዬን ይዞ ባይከራከርልኝ ኖሮ፤ ሁለት ልጆቼ የጎዳና ተዳዳሪ ይሆኑብኝ ነበር " ሲሉም ለዩኒቨርሲቲው ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና ገልጸዋል፡፡   

በአምቦ ከተማ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ምትኬ ከበደ በበኩላቸው ከባለቤታቸው ጋር በነበራቸው ክርክር ባለቤታቸው ገንዘብ ስላለው ሁለት ጠበቆች ገዝቶ በማቆም እውነታው ተቀብሮ ሊቀር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሰጣቸው አገልግሎት እውነታው ወጥቶ ከባለቤታቸው የሚደርሳቸውን ሃብት መካፈላቸውን ተናግረዋል፡፡

"ዩኒቨርሲቲው አቅም ለሌለው አቅም፣ገንዘብ ለሌለውም ገንዘብ ሆኖ የተደበቀውን እውነታችንን አውጥቶ የሚገባንን ሃብት እንድናገኝ አስችሎናል" በማለትም አመስግነዋል፡፡

ሌላዋ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሽታዬ ንጉሴ በውጪ የሕግ ማመልከቻ ለመጻፍ ከ500 ብር እንደሚጠየቅ  አስታውሰው፣ ዩኒቨርሲቲው ግን አቅመ ደካማ በመሆናቸው አገልግሎቱን እንደሰጣቸው ከምስጋና ጭምር ገልጸዋል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ምክትል ዲንና የዩኒቨርሲቲው ነጻ የህግ አገልግሎት ማዕከል አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሞሲሳ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት ለ2 ሺህ 675 ሰዎች ነጻ የህግ አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡

አገልግሎቱን ካገኙት መካከልም 1 ሺህ 451 ሴቶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

አገልግሎቱ  የምክር፣ ጥብቅና የመቆም፣ ክስ የመመስረት፣ሰነዶችንና ማመልከቻዎችን ማዘጋጀትን እንደሚያካትት ተናግረዋል ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ አንዳሉት ”ዩኒቨርሲቲው የሰጠው ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ ያወጡት የነበረ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አስቀርቷል።''

ዩኒቨርሲቲው አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረ ከ2004 ወዲህ 68 ሺህ 151 የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

አገልግሎቱ ያደረገው ድጋፍ 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም