የጥምቀት በዓልን በፍቅር፣ በመቻቻልና በመረዳዳት ማክበር ይገባል....የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት

50

ደሴ/ወልድያ ጥር 10/2011 የጥምቀት በዓልን ኢትዮጵያዊ ባህልን በሚያጎለብት መልኩ በፍቅር፣ በመቻቻልና እርስ በርስ በመረዳዳት ማክበር እንደሚገባ የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት አስታወቀ።

በወልድያ ከተማም በዓሉን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የበዓል አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መላከ ሰላም ፈንታ አበራ እንደገለጹት ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀትን በዓል ሲያከብር ኢትዮጵያዊ ባህሉን ማጎልበት በሚያስችል መልኩ በመቻቻልና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ሊሆን ይገባል፡፡

"አቅመ ደካሞችን በመርዳትና በመንከባከብ፣ አሳዳጊ ለሌላቸው ልጆች በማልበስና በማብላት በደስታ እንዲውሉ ማድረግ ከሁሉም ህዝበ ክርስትያን ይጠበቃል" ብለዋል፡፡

መላከ ሰላም ፈንታ እንዳሉት በዓሉ በሆታ፣ በዝማሬና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ ኃይሎችና ከተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በደሴ ሆጤ ስታዲየም በድምቀት እንደሚከበር ጠቁመው በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ማህበረሰቡ የሰለም አምባሳደር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ጸጋዬ በበኩላቸው " በዓሉ በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ኃይሉ እስከ ጥር 21 ቀን 2011 ድረሰ  ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል፡፡

የሰላሙ ዋና ተዋናኝ ህዝቡ በመሆኑ በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ ሁሉ ሰላሙን ነቅቶ በመጠበቅ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲገጥሙም በአቅራቢያው ለሚገኝ የጸጥታ ኃይል ፈጥኖ ማሳወቅ እንዳለበት አመልክተዋል።

ህዝበ ምዕመናኑ የጥምቀት በዓልን እንደ በፊቱ ሁሉ በሰላም፣ በፍቅርና በመቻቻል እንዲያከብር ወጣቶችን በማወያየት ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት ለማሰራት ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደተግባር መገባቱን አቶ ወንደሰን ገልጸዋል።

በደሴ ከተማ የቀበሌ 05 ነዋሪ ወጣት ተስፋሁን ዋልተንጉስ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የአካባቢው ወጣቶች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

ታቦታቱ ከየአድባራቱ ወጥተው ወደ ሆጤ ስታድየም ሲሸኙም ደካሞችን በማስቀደምና በመንከባከብ ኢትዮጵያዊ ባህልን ለማጎልበት እንደሚንቀሳቀሱ ገልጿል።

በተመሳሳይ ዜና የጥምቀት በዓልን በወልድያ ከተማ በሰላምና በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲያቆን አንተነህ ተስፋ አስታውቋል።

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወንም የአካባቢውን ማህበረሰብ ያሳተፈ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።

የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድ ያሲን በበኩላቸው "በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከበር የፀጥታ መዋቅሩ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በጥምረት እየሰራ ነው" ብለዋል።

በወልድያ ከተማ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም