ዘላቂ ሰላምን የሚያመጡ አማራጮችን እንደሚደግፉ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

76

ነቀምት ጥር 9/2011  አለመግባባቶችን በማስማማት ዘላቂ ሰላምን የሚያመጡ አማራጮችን እንደሚደግፉ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ በዞኑ ዋና ከተማ ሻምቡ  ያካሄዱትን የሰላም ኮንፍረንስ ሲጠናቅቁ ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ ላይ እንዳሉት በሆሮ ጉድሩ ዞን ጨምሮ  በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ  የሚታየው የፀጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ይፈልጋሉ፡፡

በአካባቢው የተፈጠረው አለመረጋጋት በኦነግና ኦዴፒ መካከል የተደረሰው ስምምነት በተግባር ባለመተርጎሙ የመጣ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ድርጅቶቹ አለመግባባቶችን በማስማማት  በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ህዝቡ ከሥጋት በመውጣት የራሱን ኑሮ በሰላማዊ መንገድ እንዲመራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው  ነዋሪዎቹ በአቋም መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል፡፡

የሰላም መንገዱን በመተው ኃይልን አማራጭ አድርጎ  የሚንቀሳቀስ  ክፍል የዞኑ ህብረተሰብ የማይቀበለው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ወደ ሰላም ለመምጣት ለሚፈልጉ ኃይሎች የክልሉ መንግሥት በሩን ክፍት በማድረግ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቅሰው ዘላቂ ሰላምን የሚያመጡ አማራጮችን እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

የዞኑ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ደሣለኝ ተረፈ በበኩላቸው የታጠቀው ክፍል በሰላማዊ መንገድ እጁን በመስጠት ከመንግሥት ጋር እንዲተባበሩ ለማገዝ የዞኑ  አባ ገዳዎች፣የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች መወሰናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ከዞኑ አስር ወረዳዎች የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ አባ ገዳዎች፣የኃይማኖት አባቶች ፣የአገር ሽማግሌዎች ፣የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም ነዋሪዎች መሳተፋቸውን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም