ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በፍቅርና መተሳሰብ ሊሆን ይገባል --- የኃይማኖት አባቶች

46

ሚዛን ጥር 9/2011 ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታቸው በፍቅርና መተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባ  የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ፡፡

መምህራንም ለተማሪዎች የሀገር ፍቅርና አንድነትን በትምህርት ቤቶቻቸው በሚገባ ማስተማር ችላ ሊሉት እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቴፒ ግቢ ተማሪዎችን አቀባበል ላይ የተገኙ የኃይማኖት አባቶች ለኢዜአ እንዳሉት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ የዓመታት ቆይታቸው ከቀለም ትምህርት በተጓዳኝ ግብረ ገብነትንም ማስተማር አለባቸው፡፡

በአካባቢው የኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባት መልዓከ ሰላም ቄስ ደሳለኝ መንግስቱ በሰጡት አስተያየት "ግብረ ገብነትን ማስተማር ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ለመፍጠር ያስችላል "ብለዋል፡፡

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታቸው በፍቅርና  መተሳሰብ  ሊሆን እንደሚገባ  አመልክተዋል፡፡

የትምህርት ተቋማቱም ልጆችን በመቅረጽና በመልካም ሥነ ምግባር በመግራት ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለባቸውና ተማሪዎችን በቅርበት መከታተል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች በየተቋማቸው አካባቢ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመከታተልም ልጆቹን ለአጉል ድርጊት የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን ማስወገድ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡

የእስልምና ኃይማኖት አባት ሀጂ አህመድ ሺበሺ በበኩላቸው "ወላጆች ልጆቻቸው ዕውቀትም ምግባርም እንዲማሩላቸው ለዩኒቨርሲቲዎች በአደራ ያስረከቧቸው በመሆኑ ይህንን  መፈጸም ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡

ለተማሪዎች የሀገር ፍቅርና አንድነትን በትምህርት ቤቶቻቸው በሚገባ ማስተማር ችላ ሊባል እንደማይገባም  ጠቁመው   በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ለአጓጉል ድርጊት የሚያጋልጡ ሁኔታዎችንም መቆጣጠር  እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

ለተማሪዎች ስኬትና ውድቀት የዩኒቨርሲቲ መምህራን  ትልቁን ሚና  እንደሚጫወቱ የተናገሩት ደግሞ   ቄስ ሳያ ቡክሳ ናቸው፡፡

"መምህራን በስራቸው ለሚገኙ ተማሪዎቻቸው በምግባርም በተግባርም አርዓያ በመሆን ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም" ብለዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ተማሪዎች በመልካም ሥነ ምግባር የተካኑ እንዲሆኑም የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ሀገራዊ እሴቶችን ማስተማር ይቻላል፡፡

በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው  አለመረጋጋት ተከትሎ ትምህርት ሳይጀምር የቆየው በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቴፒ ካምፓስ የተማሪዎች አቀባበል ማጠቃለያ ስነስራዓት በተያዘው ሳምንት ውስጥ መካሄዱን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም